የቀድሞ የኢትዮጵያ መብራትና ኃይል ባለስልጣን የሥልጠና ኢንስቲትዩት ተመራቂዎች የረጅም ጊዜ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የኤሌክትሪክ 761 ባች የ1978 ዓ.ም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ተመራቂዎች የተመረቁበትን 40ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።



የማህበሩ የቦርድ አባልና የዝግጅት ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ለገሰ ዳበሳ እንደገለጹት ፕሮግራሙ በሀገር ውስጥና በውጭ በተለያየ ሁኔታ ላይ የሚገኙ የቀድሞ ተመራቂዎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር ያላቸውን ልምድና እውቀት በመጠቀም በቀጣይ ከተቋማቱ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች አብሮ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት ለማሳየት ያለመ ነው።
ተመራቂዎቹ ከዲዝል ኃይል ማመንጫዎች ጀምሮ በተመደቡባቸው የሥራ ቦታዎች ሁሉ ፈተናዎችን ተቋቁመው ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን ተቋማቱ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የማይተካ ሚና ማበርከታቸውን አስታውሰዋል።
የሁለቱ ተቋማት ሥራ አስፈጻሚዎች የማህበሩ የበላይ ጠባቂ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ለገሰ በቀጣይ አቅማቸውን በማሰባሰብ እና ልምዳቸውን በመጠቀም እንዲሁም ከሌሎች መሰል ማህበራት ጋር በመተባበር በዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ተመራቂዎቹ ለአዳዲስ ሠራተኞች የነበራቸውን ሙያ በማስተላለፍ እና ሥልጠናዎችን በመስጠት በኩል ተቋማቱን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳና የቀድሞው መምህር አቶ ቦጋለ ፈይሳ በበኩላቸው የቀድሞ ተመራቂዎች የሙያ ልደታቸውን ማክበራቸው ለሌሎች ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


ተመራቂዎቹ በተለያዬ ሁኔታዎች ላይ የሚገኙ ቢሆኑም ትምህርት የማያቋርጥ ሂደት በመሆኑ በረጅም ጊዜ ያገኙትን እውቀትና ልምድ በማስተባበር ለተቋማቱና ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኢንስቲትዩቱ የተለያየ ዓመት ተመራቂዎች እና የመብራት ኃይል የጡረተኛ ሠራተኞች ማህበር ተወካዮችም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በቀጣይ ከኤሌክትሪክ 761 ባች ጋር በመተባበር የተሻለ ሥራ ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የፕሮግራሙ ተሳታፊ የቀድሞ ተመራቂዎች በበኩላቸው ከኢንስቲትዩቱ ያገኙት የተግባርና የንድፈ ኃሳብ ዕውቀት አሁን ለደረሱበት መሠረት መሆኑን ገልፀው ለዚህም መምህራኖቻቸውንና ተቋማቱን አመስግነዋል፡፡
በዕለቱ ጡረታ ለወጡ አባላት እውቅና የተሰጠ ሲሆን በተለያዩ ምክንያት በሕይወት ለሌሉ የኢንስቲትዩቱ የኤሌክትሪክ 761 ባች አባላትም የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”






