የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ካቀረበው የኃይል ሽያጭ 67 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን የ2018 በጀት የግማሽ ዓመት እቅድ አፈጻጸም በዛሬው ዕለት ገምግሟል።
በግምገማው ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መለስ መና አንደገለጹት የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ተቋማቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን በማዘመን ለሕብረተሰቡ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አለበቸው።
ከለውጡ በኋላ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከነበረባቸው ውስብስብ ችግሮች ወጥተው ትርፋማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በሁለቱ ተቋማት መካከል የለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር ለሕብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የአገልግሎት አሰጣጡን ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ የሥነ-ምግባር ችግር ያለባቸውን ባለሙያዎች በሕግ እንዲጠየቁ በማድረግና በተሻለ አቅም ሕብረተሰቡን የሚያገለግሉ ሠረተኞችን ማበረታታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ኢንጅነር ሰለሺ ኮሬ (ዶ/ር) የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማሳደግ ምክር ቤቱ ለተቋማቱ የተሻለ በጀት ሊመደብላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተቋማቱ የሚገነቡ የኃይል መሠረተ ልማት አውታሮችን ከስርቆት ለመከለል በየደረጃው ካሉ የአስተዳደር እና የሕብረተሰብ ክፍሎች ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
ተቋማቱ የሚያደርጉት የግዥ ሂደት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር መዘርጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ ባለፉት ስድስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት በተደረገው የኢነርጂ ሽያጭ ተቋሙ 67 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ማገኘቱን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል።
ተቋሙ በየአካባቢው ለሚነሱ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና የኃይል መሠረተ ልማት ግንባታዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ነው ብለዋል።
የኃይል ስብጥሩን ለማመጣጠንና አቅርቦቱንም ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ በትብብር እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
ምንጭ፦ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




