በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህብረት ስምምነት እና ሌሎች የአሰራር መመሪያዎች አማካኝነት የሴት ሰራተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን የተቋሙ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች መምሪያ ገለጸ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ እንደተገሩት ማሻሻያዎች ከመደረጋቸው በፊት ሴቶችን በፍትሀዊነት አሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮች ባለመዘርጋታቸውና የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ በየደረጃው ያለው የሴት ሠራተኞች ቁጥርና የተሳትፎ ሁኔታ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡
በአሁኑ ወቅት በህብረት ስምምነቱና ሌሎች የተቋሙ የአሰራር መመሪያዎች ላይ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮች በመካተታቸው የተሻሉ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በዚህም ከ2013 ዓ.ም በፊት በተቋሙ 14 በመቶ የነበረውን የሴት ሠራተኞች ድርሻ ወደ 17 በመቶ እንዲሁም በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች 9 በመቶ የነበረውን 11 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ሴቶች ሥራቸውን ተረጋግተው እንዲሰሩ በዋናው መ/ቤት እና በአዳማ 1 የንፋስ የኃይል ማመንጫ የህጻናት ማቆያ መቋቋሙን አስታውሰው በቀጣይም በሌሎች የሥራ አካባቢዎች የሕጻናት ማቆያ ለማቋቋም በእቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡
የሴቶችን የአመራር ክህሎት ለማጎልበትና የውሳኔ ሰጪነት አቅም ለማዳበርም ተቋሙ በቀረጸው የልዩ ድጋፍ መሰረት በየዓመቱ 55 ሴት ሠራተኞች ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ድግሪ ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መመቻቸቱን ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡
የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መምሪያው ከሁሉም የሥራ ክፍሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በህብረት ስምምነቱና በሌሎች የተቋሙ መመሪያዎች ላይ የድጋፍ እርምጃው ያስፈለገው ሴቶች ተደራራቢ ኃላፊነቶች ያሉባቸው መሆኑን ተገንዝቦ ሁሉም አመራርና ሠራተኛ ለመመሪያዎቹ መፈፀም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”