በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በራስ አቅም የተገነቡ 13 ፕሮጀክቶች ተጠናቀዋል

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በራስ አቅም የተገነቡ 13 ፕሮጀክቶች ተጠናቀዋል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዘርፍ የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 13 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሥራ ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ኃ/ጊዮርጊስ እንዳስታወቁት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በመምሪያው ስር በሚገኙ የሥራ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ 28 ፕሮጀክቶች የግንባታ ሥራ ሲከናወን ነበር።

ከእነዚህ ውስጥ መምሪያው በበጀት ዓመቱ የ18 ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ አቅዶ 13ቱን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግረዋል፡፡

ቀሪዎቹ አምስት ፕሮጀክቶች በፀጥታ እና በዕቅዱ ያልተያዙ ተጨማሪ ሥራዎች በመምጣታቸው ምክንያት በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት አለመጠናቀቃቸውን ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ የአዋሽ 2 እና 3 ማመንጫ ጣቢያዎች የአፈር መሸርሸር መከላከያ፣ የራይቱ – ጎዴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር የሁለት ምሶሶዎችን ቦታ የመቀየር፣ የሆለታና ሰበታ ዕቃ ግምጃ ቤት ሥራዎች ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በበጀት ዓመቱ ከተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች ውስጥ አምስቱ በፕሮጀክት ማኔጅመንት አንድ ቢሮ፣ ሦስቱ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ሁለት እንዲሁም አምስቱ በሲቪል ጥገና ቢሮ የተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በተያዘላቸው መርሃ ግብር ካልተጠናቀቁ አምስት ፕሮጀክቶች መካከል አራቱ አፈፃፀማቸው ከ85 በመቶ በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

አቶ ሰለሞን እንዳሉት መምሪያው በዕቅድ ከያዛቸው ሥራዎች በተጨማሪ ኦፕሬሽን ላይ ባሉ ከፍተኛ የማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የጥገና እና የሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሥራዎችን አከናውኗል፡፡

የፕሮጀክቶቹ የግንባታ ሥራ በራስ ኃይል መከናወኑ የሠራተኛውን የእኔነት ስሜት በማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሪንና ተጨማሪ ወጪን በማስቀረት እንዲሁም ለሀገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በራስ አቅም በተከናወኑ ሥራዎች ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመምሪያው እየተከናወኑ ከሚገኙ 15 ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት የሦስት ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሥራ ለመጀመር ዕቅድ መያዙንም አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top