የሳፕ ፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል ሲተገበር የጥገናና ኦፕሬሽን ስራዎችን ያዘምናል

የሳፕ ፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል ሲተገበር የጥገናና ኦፕሬሽን ስራዎችን ያዘምናል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጥገናና ኦፕሬሽን ሥራዎች ለማዘመን በተዘጋጀው የፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል ላይ ለሁሉም የሪጅን ዳይሬክተሮች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን በኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፊያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የቴክኒካል ድጋፍ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት መላኩ እንደገለፁት የማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና የማስተላለፊያ መስመሮችን ኦፕሬሽንና ጥገና ለማሳለጥ የሚያግዝ የፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና መሰጠት ተጀምሯል፡፡

ሥልጠናው የሳፕ ፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁልን ተግባራዊ በማድረግ የሪጅኖችን የአሰራር ሥርዓት ለማዘመን፣ ጠንካራ የሀብት ቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ወጭ ለመቀነስ እና ሥራን ለማቀላጠፍ አስተዋፅኦው ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቢሮው ኤሌክትሪካል መሀንዲስ እሌኒ ሲሳይ በበኩላቸው የፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል የማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ንብረቶች የሚመዘግብ ከመሆኑም ባሻገር የጥገና ሥራዎችን በዕቅድ ላይ ተመስርቶ ለማከናወን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ሥልጠናው ሪጅኖች የጥገና ሥራዎቻቸውን በምን መልኩ በሳፕ ፕላንት ሜንቴናንስ እንደሚያካሂዱ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ ከሪጅኖች የተውጣጡ እና ለፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል ጠቃሚ ዳታዎችን ሲሰበስቡ የነበሩ ባለሙያዎችና የሪጅኖቹ የጥገና ባለሙያዎች ጨምሮ በተዋረድ እስከ ታች ድረስ ሥልጠናው እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ሁለት ሥር ለሚገኙ የማከፋፊያ ጣቢያ ኃላፊዎች የሳፕ ፕላንት ሜንቴናንስን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

በዘርፉ የሳፕ ትግበራ ኮሚቴ አባል አቶ ወልዳይ ገብረትንሳዔ እንደተናገሩት ሥልጠናው የጣቢያ ኃላፊዎች የሳፕ ፕላንት ሜንቴናንስን ተግባራዊ በማድረግ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን ለማቀላጠፍና ለማዘመን ያግዛቸዋል፡፡

የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ቢኒያም ጸጋዬ በበኩላቸው የሳፕ ፕላንት ሜንቴናንስ መተግበር በጣቢያዎቹ በማንዋል የሚሰሩ አሰራሮችን በማስወገድ ጊዜንና ወጭን ብሎም የመብራት መቆራረጥ ድግግሞሹን በቀነሰ መልኩ ሥራዎችን ለማከናወን ይረዳል ብለዋል፡፡

አስተባባሪው አክለውም የጥገና ሥራዎች በሲስተም የተደገፈ የመረጃ ሥርዓት እንዲኖራቸውና ወጥ አሰራር እንዲተገበር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ሥልጠናዎቹ በኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፊያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ቴክኒካል ድጋፍ ቢሮ ከሰው ኃይል ስልጠናና ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጁ ናቸው፡፡

ለአስር ቀናት የሚቆየው ሥልጠና በጥገና የአሰራር ሥርዓት፣ በመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት እና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top