በኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የዕቃ ግምጃ ቤቶች ላይ የካይዘን የአሰራር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ ዊ ቢውልድ ኩባንያ ገለፀ።
በኩባንያው የዕቃ ግምጃ ቤቶች ሱፐርቫይዘር አቶ በርገና ባዴቦ እንደገለፁት ለፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ የሚያገለግሉ ግብዓቶች፣ ለሥራ ላይ ደህንነት መሳሪያዎች እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የመለዋወጫ ዕቃዎች ተለያይተው በካይዘን ፍልስፍና የአሰራር ስርዓት መሠረት በአግባቡ ተደራጅተዋል።
ይህም የዕቃዎቹን ደህንነት በማረጋገጥና ሥራ ተቋራጩን ከአላስፈላጊ ወጭ በማዳን የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ማድረጉን ነው ያስታወቁት።
ለፕሮጀክቱ ሥራ የሚያስፈልጉ ዕቀዎች በፕሮጀክቱ ዕቃ ግምጃ ቤት በዓይነታቸው እና በገቡበት ጊዜ ተለይተው እንደሚቀመጡም አቶ በርገና ተናግረዋል።
ዕቃ ግምጃ ቤቱ ላይ የሚደራጁ ዕቃዎች በሚሰጣቸው መለያ መሠረት በዳታ ቤዝ ተመዝግበው እንደሚቀመጡ ጠቁመው ይህም በግምጃ ቤቱ ያሉ እና ወጪ እንዲሆኑ የሚጠየቁ ዕቃዎችን ክትትል ለማድረግና ለጠያቂው አካል በቀላሉ ለማቅረብ ማስቻሉን አመልክተዋል።
እንደ ሱፐርቫይዘሩ ገለፃ ግምጃ ቤቶቹ በካይዘን የአሰራር ስርዓት መሠረት መደራጀታቸው ሥራዎችን ለማቀላጠፍ እና ዕቃዎችን ከተለያዩ ጉዳቶች በመጠበቅ በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
አቶ በርገና እንዳሉት በካይዘን ፍልስፍና መደራጀቱ ዕቃ ወጪ ሲደረግ ዕቃዎችን ለመፈለግ የሚወስደውን ጊዜ ለማስቀረት እና አዲስ የሚገቡ ዕቃዎች በማን እንደታዘዘ፣ ለምን ዓላማ እንደሚውል እና ዕቃዎቹን ለአዘዘው አካል በአግባቡ ለማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በዕቃ ግምጃ ቤቶቹ ላይ በየስድስት ወሩ ቆጠራ እንደሚከናወን ያነሱት ሱፐርቫይዘሩ ይህም የጎደሉ ዕቃዎችን በቀላሉ በመለየት ለማሟላት እና የሚገቡ ዕቃዎችን በዓይነታቸው ለማስቀመጥ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ድርጅቱን ከአላስፈላጊ ወጪ ለመታደግ ቀድመው የገቡ ዕቃዎች ጥቅም ላይ ሳይውሉ አዲሶቹን መጠቀም እንደማይቻል ሱፐርቫይዘሩ አስረድተዋል።
ሥራውን በአግባቡ ለማከናወንና ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጅ ጋር ለመራመድ በዕቃ ግምጃ ቤቱ ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች ሙያዊ ስልጠናዎች በኩባንያው እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ካይዘን ለዕይታ ማራኪ የሥራ ቦታ እንዲኖር የሚያስችል ወጪ፤ ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥብ ከጃፓን የተቀዳ የአሰራር ሥርዓት ፍልስፍና ነው።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”