በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የተከናወኑ የጥገና ሥራዎች አስተማማኝ ኃይል ለማምረት አስችለዋል

በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የተከናወኑ የጥገና ሥራዎች አስተማማኝ ኃይል ለማምረት አስችለዋል

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ የጥገና ሥራዎች የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች አስተማማኝ የኃይል ምርት እንዲያመርቱ ማስቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ የቴክኒካል ድጋፍ እና አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ባይለየኝ እንዳስታወቁት በ2016 በጀት ዓመት በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የኃይል ምርቱን አስተማማኝ የሚያደርጉ የቅድመ መከላከል፣ የፍተሻ እና የትንበያ ጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በዚህም የኃይል ማመንጫዎች ጣቢያዎችን ዝግጁነት አፈፃፀም 94 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በግልገል ጊቤ 2 እና 3፣ መልካ ዋከና፣ ጣና በለስ፣ ፊንጫ፣ ተከዜ፣ ረጲ፣ ቆቃ እንዲሁም አዳማ 1 እና አሸጎዳ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ጨምሮ በሁሉም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ዓመታዊ የጥገና ሥራዎች እና የፍተሻ ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ የጥገና ሥራዎች መከናወናቸው የማያቋርጥ እና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት ማስቻሉንና በዚህም በ2015 በጀት ዓመት ከነበረው የኃይል ምርት በ16 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለጣቢያዎቹ የጥገና ሥራ የሚያስፈልጉ የመለዋወጫ ዕቃዎች ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በተደረገ ስምምነት መሰረት እና በተለያዩ መንገዶች መቅረቡንም አስታውሰዋል፡፡

እንደ አቶ ዘላለም ገለጻ በበጀት ዓመቱ ከጥገና ሥራዎች በተጨማሪ የጣቢያዎቹን የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራ ለማዘመን የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
          
በዚህም የበለስ፣ ግልገል ጊቤ 1 እና 2 ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ስካዳ ለማሻሻል እና ለማዘመን አንድሪዝ ሃይድሮ እና ቮይት ሃይድሮ ከተባሉ ኩባንያዎች ጋር ውል ተፈርሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ዘላለም አክለውም በጊቢ 3 ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የመረጃ አያያዙን ለማዘመንና የእያንዳንዱን ማሽን ታሪክ በተገቢ ሁኔታ ለማደራጀት እንዲሁም በሥራ ቦታው ላይ የማሽኑን ማኑዋል፤ የጥገና ታሪክ እና ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ችግሮችን በሳይት ለሁሉም ቴክኒካል ሠራተኛ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መተግበሩንም ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት 20 ሺ 596 ነጥብ 38 ጌጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ተችሏል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top