
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጥናት ከለያቸው ተቋማዊ ስጋቶች መካከል 62 በመቶዎቹ ላይ እርምጃ መውሰዱን የኮርፖሬት ስጋት ፋይናንስና ኢኮኖሚ መምርያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ እንዳለ ማሞ እንደገለጹት መምረያው በ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ የተቋሙን ስጋቶች ለመለየት የሚያስችል ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡
በጥናቱ መሰረት ከአሁን ቀደም በሁሉም የሥራ ሂደቶች ከተለዩ 138 የተቋም ስጋቶች በተጨማሪ 16 አዳዲስ ስጋቶች ተለይተዋል ብለዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የተለዩት ስጋቶች ከፋይናንስ፣ ከመደበኛ ሥራ፣ ከሰው ኃይል፣ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ከዕቃ አቅርቦት፣ ከሥራ ላይ ደህንነት፣ ከሕግ እና ደንብ፣ ከተቋሙ ውጭ በሆኑ ምክንያቶች እና ከግል አልሚዎች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
ከተለዩት ስጋቶች መካከል 111 የሚሆኑት የስጋት ደረጃቸው ከፍተኛ በመሆኑ በ 79 ስጋቶች ለይ እርምጃ እንደተወሰደና ቀሪ 32 ስጋቶችን በቀጣይ ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተቋም ስጋቶች ተብለው የተለዩ ጉዳዮች በተቋሙ ሁሉም የሥራ ሂደቶች ሲገለፁ 154 ቢደርሱም በዋና ዋና ስጋቶች አንፃር በዘጠኝ መደቦች የተጠቃለሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በዘጠኙ መደብ በጥናት ከተለዩት ስጋቶች መካከል 62 በመቶዎቹ ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን እንዲሁም የሰጋት ደረጃቸው ከፈተኛ የነበሩት ስጋቶች ላይ በአማካኝ 71 በመቶ እርምጃ ተወስዷል፡፡
ተቋሙ ጊዜውን የጠበቀና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ስጋቶችን በመለየት፣ በመከታተል እና መረጃዎችን በማደራጀት ለውሳኔ ሰጪ አካላት በተሳለጠ መልኩ ለማቅረብ የሚያስችሉ ዘመናዊ አሰራሮችን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኦሪን ኮንሰልቲንግ እና ኢሰሪ ኢስተርን አፍሪካ ከተባሉ ድርጅቶች ጋር እየተገበረ መሆኑንም አስታወቀዋል፡፡
በተጨማሪም ስጋቶቹ ዳግመኛ እንዳይከሰቱ የማስወገድ፣ በተቋሙ ሊፈቱ የማይችሉ ስጋቶችን ወደ ሶሰተኛ ወገን የማሰተላለፍ፣ በተቋም ስጋት ማቅለያ መንገድ ስጋቶችን የማስወገድ እና ተቋሙን ጫና የማይከቱትን መቀበል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስትራቴጅ ተቀርጾ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡
የስትራቴጅው መተግበር የተቋሙን የስጋት ሁኔታ በመገምገም ባለድርሻ አካላት ተቋሙን የሚያግዙ መመርያዎችና ህጎችም እንዲወጡ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ እንዳለ እንዳሉት ከተቋሙ ሁሉም የሥራ ክፍሎች የተወጣጡ ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ከኮርፖሬት አመራር ጋር የሚገናኝ የስጋት ባለቤት ተዋቅሮ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በአዲሰ አበባ ዩንቨርስቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ይህም ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማሳደግ በየሥራ ክፍሉ ያሉ የተቋም ስጋቶችን በመለየት መፍትሄ ለመስጠት ጉልህ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”