
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት በዞኑ በተከሰተው ተፈጥሯዊ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ድጋፍ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የአደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን በኩል በዛሬው ዕለት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም በዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በኩል ለተጎጂዎች እንዲደርስ የአንድ ሚሊየን ብር ቼክ ለኮሚሽኑ አስረክቧል።
በእርዳታ ርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል እንደገለፁት በዞኑ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሳቢያ የበርካታ ወገኖቻችን ህይወት በማለፉ አዝነናል።
በአስተዳደሩ ስር የሚገኙት ተጠሪ ተቋማት ከሚሰሯቸው የንግድና የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን በርካታ የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
አስተዳደሩና ተጠሪ ተቋማቱ በዞኑ ተከስቶ በነበረው ተፈጥሯዊ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል የ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
በቀጣይም ጉዳት የደረሰባቸውን የማህበረስብ ክፍሎች በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዳደሩና ተጠሪ ተቋማቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፉን ከአስተዳደሩና ከተጠሪ ተቋማቱ የተረከቡት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የአደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተ/ማሪያም (ዶ/ር) እንደገለፁት በዞኑ ሁለት ቀበሌዎች ላይ በደረሰው አደጋ የ243 ሰዎች ህይወት አልፏል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በዘላቂነት ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማቱ ላደረጉት የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ጉዳት በደረሰባቸው የዞኑ ነዋሪዎችና በኮሚሽኑ ሥም ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




