በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የግድቡን ደህንነት ለመጠበቅ እና አስተማማኝ የኃይል ምርት ለማቅረብ ያስቻሉ የጥገና ሥራዎች በጣቢያው ሠራተኞች መከናወናቸውን የግልገል ጊቤ 1 የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ገለጸ።
በጣቢያው የጥገና ክፍል ኃላፊ አቶ ታምሩ ለገሰ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በጣቢያው የጥገና ክፍል ሠራተኞች ሳምንታዊ እና ወርሃዊ የቅድመ መከላከል፣ የፍተሻ፣ የትንበያና የሁኔታ አመላካች ጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።
የጥገና ሥራዎቹ በተርባይኖች፣ በግድቡ፣ በስዊችያርድ 15 ኪሎ ቮልት መስመር፣ በጣቢያው የተፋሰሰ ስርዓት እና በ15 ኪሎ ቮልት ስዊችጊር ፓኔል ላይ መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በጣቢያው ሶስቱም ዩኒቶች ላይ ዓመታዊ የፍተሻ እና ጥገና ስራዎች እንዲሁም የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች ተከናውነዋል።
እንደ አቶ ታምሩ ገለፃ ስርቆት ተፈጽሞበት የነበረውን የግድቡ የውሃ መቆጣጠሪያ እና የኮሙዩኒኬሽን ኬብል እንዲሁም ከግድብ ስዊችያርድ የሚሄደው 15 ኪሎ ቮልት መስመር እና የወደቁ 5 ታወሮችን በከፍተኛ ርብርብ በመጠገን ወደ አገልግሎት ማስገባት ተችሏል ብለዋል።
የጥገና ሥራዎች በጣቢያው የጥገና ሠራተኞች አቅም መከናወኑ የተናገሩት አቶ ታምራት ይህም ተቋሙን ከከፍተኛ ወጭ ከማዳኑም በላይ ሠራተኞች አዳዲስ ልምድ እንዲያገኙ እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የተከናወኑት የጥገና ሥራዎች የኃይል ማመንጫ ግድቡን ደህንነት በመጠበቅ እና የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማሳለጥ የኃይል ምርቱ አስተማማኝ እንዲሆን ማድረጉን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ታምሩ ገለጻ በዝናብ ወቅት ከፍተኛ የኃይል ጭነት በማስተናገድ ግድቡ ሞልቶ እንዳይፈስና በበጋ ወቅት የግድቡ ውሃ እንዳያልቅ የኃይል ጭነት በማመጣጠን የግድቡን ውሃ በአግባቡ መጠቀም የሚስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
184 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የግልገል ጊቤ 1 የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”