የሥነምግባር ግንባታ በሥልጠና ብቻ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በተቋሙ ውስጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚተገበር ሂደት መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥነ-ምግባርና ፀረ- ሙስና መከታትያ መምሪያ ገለጸ።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አጥናፌ “የሥራ ቦታ ሥነ-ምግባር” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ለተቋሙ ሠራተኞች ሥልጠና ሰጥተዋል።
ሥልጠናው የሠራተኛውን ግንዛቤ በማሳደግ ከጥቅም ግጭት እና ምስጢር ጠባቂነት እንዲሁም ከመረጃና ከሪፖርት ትክክለኝነት፣ ከስጦታና መዝናኛ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ የሥነ-ምግባር አጣብቂኞችን በመለየት አስተማሪ የሆነ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማስቻል ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
በተቋሙ ግልጽ የሥነ-ምግባር መርሆችና ፍትሐዊ አሠራሮችን የሚያሰፍኑ እንዲሁም የጥቅም ግጭትን የሚከላከሉ ሥርዓቶችና የሚያጋጥሙ የሥነ-ምግባር ጥሰቶችን በአግባቡ የሚያስተናግዱ ሥርዓቶች መዘርጋት ይገባል ብለዋል።



ጠንካራ የሥነ-ምግባር ባህል ያለው ተቋም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሠራተኛው ለሕግና ሥርዓት ተገዥ በመሆን ሥራዎችን በመልካም ምግባር ማከናወን እንዳለበትም አብራርተዋል።
ሠራተኛው ማንኛውንም ውሳኔ ሲወስንም ሆነ ተግባሩን ሲያከናውን ከተቋሙ ቁልፍ ተልዕኮ አንጻር መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የሥራ ቦታ ሥነ-ምግባር በቃል ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በዕለት ከዕለት ተግባር የሚረጋገጥ በመሆኑ ሁሉም በኃላፊነትና በባለቤትነት ስሜት መሥራት አለበት ብለዋል።
ሠራተኛው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን የተቋሙን እሴቶች በመከተል የራስንና የተቋሙን መልካም ስም በሚጠብቅ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሠላምን በሚያሰፍን አግባብ ሊጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።


