ሁሉም ሠራተኛ በተሰማራበት የሥራ መስክ የተቋሙ አምባሳደር መሆን ይጠበቅበታል

ሁሉም ሠራተኛ በተሰማራበት የሥራ መስክ የተቋሙ አምባሳደር መሆን ይጠበቅበታል

የተቋሙን ገጽታ ለመገንባት ሁሉም ሠራተኛ በተሰማራበት የሥራ መስክ የተቋሙ አምባሳደር መሆን እንደሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።

“የሠራተኞች ተሳትፎ ለተቋማዊ ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ለተቋሙ ሠራተኞች ሲሰጥ የቆየው ሁለተኛ ዙር ሥልጠና በዛሬው ዕለት ተጠናቋል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ተወካይ ዶ/ር ግርማ ግዛቸው እንደገለጹት አሁን ያለውን ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ተወዳዳሪና ብቁ ባለሙያ ለመሆን ሠራተኛው ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልም የተቋሙ ሠራተኛ ቀጣይ ጊዜንና ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደጉማ ነዳ ሥልጠናው በዕለት ከዕለት ሥራዎቻችን የሚያጋጥሙንን ችግሮች በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ለመፍታትና ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

ሠራተኛው መብትና ግዴታውን አውቆና የሥራ ሥነ-ምግባርን ተላብሶ በመፍጠርና በመፍጠን ውጤት ለማስመዝገብ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንደሚረዳም ገልጸዋል።
የሠው ሀብት አስተዳደር ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተማም አፍደል በበኩላቸው ተቋሙ የሠራተኛውን ተሳትፎ ለማሳደግና ሁሉን አቀፍ ውጤት ለማስመዝገብ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አዳዲስ ለሚገቡ ሠራተኞች የሚሰጥ የመግቢያ ሥልጠና ቢኖርም የሕብረት ስምምነቱን ጨምሮ ሌሎች የሙያ ሥልጠናዎችን ጨምሮ በቀጣይ በተለያዩ የኮሙዩኒኬሽን ዘዴዎች በስፋት ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ተቋሙን ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ የብራንድ ማሻሽያ ሥራዎች መጀመራቸውን የጠቆሙት የሥራ ኃላፊዎቹ ሆኖም የተቋሙን ገጽታ የመገንባት ሥራ የአንድ ክፍል ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም ሠራተኛ በተሰማራበት የሥራ መስክ የአምባሳደርነት ሚናውን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

መሰል ሥልጠናዎች መዘጋጀታቸው ሠራተኛው መብትና ግዴታውን እንዲሁም የተቋሙን አሁናዊ ቁመና በውል ተገንዝቦ ሥራዎችን ሥነ-ምግባራዊ መርሆችን ማዕከል አድርጎ በማከናወን ለተቋሙ ስኬት በህብረት እንዲነሳ የሚያስችል መሆኑን የሥልጠናው ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

Scroll to Top