በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማረጋገጥና ጠንካራ ተቋማዊ ባህልን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ።
ተቋሙ “የሠራተኞች ተሳትፎ ለተቋማዊ እድገት ” በሚል መሪ ሀሳብ ለሠራተኞቹ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የሦስተኛው ዙር ስልጠና ተጀምሯል።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በተቋሙ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ጽዮን በቀለ እንደተናገሩት በተቋሙ የሠራተኞችን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ ውጤት ለማምጣት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ለሁለት ቀናት የሚሰጠው ስልጠና በሠራተኞች ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም በሥራ ቦታ ሥነ- ምግባር፣ የሠራተኞችን ተሳትፎ ለማጠናከርና ጠንካራ የሆነ ተቋም ለመገንባት ያለመ እንደሆነም ገልፀዋል።
በተቋሙ የተጠያቂነት ሥርዓትን ለማረጋገጥና ጠንካራ ተቋማዊ ባህልን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑ በመግለፅ ይህ ስልጠና አንዱ ማሳያ መሆኑንም ሥራ አስፈፃሚዋ አንስተዋል።
ከስልጠናው እውቀትን ለማስፋፋት ብቻ ሳይሆን በተቋሙ ውጤት ለማስመዝገብ፣ የተጠያቂነት ሥርዓትን እና ተቋማዊ ባህልን ለማሻሻል ሥራዎቹን ሥነ- ምግባርን ባከበረ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግም ወ/ሮ ጽዮን አስገንዝበዋል።
ሁሉም ስልጠናውን በንቃት በመከታተልና ያገኘውን እውቀት በሥራ ቦታው ላይ ተግባራዊ በማድረግ ለተቋሙ ስኬት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
በስልጠናው ላይ ስለ ሠራተኞች ተግባርና ኃላፊነት፣ በተቋሙ ስትራቴጂካዊ መነሻዎች ፣በደንበኞችና ባለ ድርሻ አካላት አያያዝ፣ በተቋማዊ ባህል ግንባታ፣ በሥራ ላይ ደህንነት፣ በሙያዊ ሥነ ምግባርና ታማኝነት እንዲሁም በአፈፃፀምና ቀጣይነት ባለው መሻሻል ላይ ትኩረት ያደረጉ ጉዳዮች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።


በተጨማሪም በሥራ ቦታ ሥነ- ምግባር ምንነትና መርሆች፣ በሥነ- ምግባር አጣብቂኞች፣ የሥነ- ምግባር ውሳኔ አሰጣጥ ማዕቀፎችና አቅጣጫዎች፣ የሥራ ሥነ- ምግባር ለተቋም ስለሚኖረው ሚና እንዲሁም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ አጠቃቀም በተቋም ላይ ምን መምሰል እንዳለበት የሚዳስሱ ርዕሰ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።



