በኃይል ዘርፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመፍታት ተቋሙ በለያቸው አራት ሙያዎች ላይ የሙያ ደረጃና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ለማስጀመር የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ መካሄዱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮ ፓወር አካዳሚ አስታወቀ፡፡
የፓወር አካዳሚው ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት የውይይት መድረኩ በተለዩት ሙያዎች ላይ የሙያ ደረጃና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ለማስጀመርና ለባለሙያዎቹ በዝግጅቱ ዙሪያ የመግቢያ ሥልጠና ለመስጠት ያለመ ነው፡፡
ተቋሙ ብቸኛ ኃይል አቅራቢና አስተላላፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዘርፉ ልምድ ያለውና የሰለጠነ ብቁ ባለሙያ ከሌላ ቦታ ሊያገኝ የሚችልበት ዕድል አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች ተመርቀው ተቋሙን የሚቀላቀሉ የቴክኒክ ባለሙያዎች ብቃትም ዘርፉ ከሚፈልገው አንፃር ክፍተቶች መስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
የተቋሙ ከፍተኛ አመራር ይሄን የአቅም ክፍተት ለመቅረፍና ዘርፉ የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሠው ኃይል ለማፍራት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህም ከትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ለቴክኒሽያኖች የሚሰጡ ሥልጠናዎችና የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት (ካሪኩለም) የሚከለስበትና ከዘርፉ ጋር የሚሄድ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡
ከተቋሙ የጀነሬሽን ቢዝነስ እና ትራንስሚሽን ቢዝነስ ጋር የተያያዙ አራት ሙያዎችን በመለየት የሙያ ደረጃና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ለማከናወን የ35 ባለሙያዎች ልየታና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውንም አብራርተዋል፡፡



በቀጣይም በሙያዎቹ የሥልጠና ማንዋልና የምዘና ሥርዓት ዝግጅት እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
የግል አልሚው በኃይል ዘርፉ ተሳታፊ የሚሆንበት ዕድል እየተፈጠረ በመሆኑ የሰው ኃይል ፍላጎቱ እያደገ መሄዱ የማይቀር ነው ያሉት ዶ/ር ወንድወሰን የሙያ ደረጃና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅቱ በዘርፉ ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ያስችላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የቴክኒክና ሙያ እና የሥልጠና ተቋማት የኃይል ዘርፉን ልዩ ሁኔታ እና የተቋሙን ፍላጎት ከግምት ባስገባ መልኩ ባለሙያዎችን እንዲያበቁ እና የተቋሙ የፓወር አካዳሚው በዘርፉ ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችለውን ዕውቅና እንዲያገኝ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም የሙያ ደረጃና የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት የሚሳተፉ ባለሙያዎች በጊዜ የለኝም መንፈስ ሥራውን በአጭር ጊዜ በጥራት እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የስርዓተ ትምህርትና የሥልጠና መሣሪያዎች ባለሙያ የሆኑት አቶ መሳይ ያዕቆብ ሚ/ር መ/ቤቱ በሌሎች ሙያዎች የዓለም አቀፍ ልምዶችን በመቀመር ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ የሚሰጡ ሥልጠናዎችም ዓለም አቀፍ መስፈርቶችንና መሣሪያዎቹ የጠበቁና የተቋሙን ፍላጎት ያሟሉ እንዲሆኑ በትብብር ለመስራትና ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡



በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሙያ ደረጃ ምደባ ባለሙያ አቶ ተመስገን ማሞ በበኩላቸው በኃይል ዘርፉ ለተለዩ ሙያዎች የሙያ ደረጃና ሥርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱ የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ያስችላል ብለዋል።
የተቋሙን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚችልና የበለጠ ምርታማ የሆነ ባለሙያ ለማፍራት የሀገር ውስጥና የውጭ ልምዶችን ያካተተ ሰነድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

