በአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞችን ጤናና የሥራ ደህንነት ለመጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ አስታወቀ፡፡
የተቋራጩ ሲመንስ ጋሜሳ ኩባንያ የአካባቢ፣ የሥራ ቦታ ጤናና ደህንነት አማካሪ አቶ ቻላቸው ሽፈራው እንደተናገሩት በፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሠራተኞች የሥራ ደህንነታቸውና ጤንነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
ከፕሮጀክቱ ባህርይና ከማሽነሪዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ሠራተኞች ለአደጋ ተጋላጭ እንደሚሆኑ በመገንዘብ የሥራ ስጋት ምርመራ መከናወኑንም አንስተዋል፡፡
በዚህም የጤናና የአደጋ ሥጋቶችን በመለየት አደጋዎችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል አሰራሮችን በመዘርጋት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡
ስለ አሰራር ሥርዓቱ፣ ስለ አደጋ አጋላጭ ሁኔታዎች እና አደጋን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ለሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚሠጥ አማካሪው አስረድተዋል፡፡
እንደ ሥራው ባህሪ ለሠራተኞች የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች እንደሚቀርቡና በአተገባበሩ ላይም ክትትል እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ቻላቸው ገለፃ በፕሮጀክቱ ላይ ለሚያጋጥሙ አደጋዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የመጀመሪያ እርዳታ መስጫ ማዕከል ከማቋቋም ጀምሮ የጤናና ከፍተኛ አደጋዎች ሲከሰቱ ሠራተኛው የህክምና አገልግሎት የሚያገኝበት አሰራር ተዘርግቷል፡፡
ሠራተኛው የሥራ ላይ ደህንነት ህጎችን ባህል በማድረጉ እስከ አሁን ባለው የግንባታ ሂደት ከቀላል ጉዳቶች ውጭ ምንም አይነት የከፋ ጉዳትና ሞት ሳይከሰት ፕሮጀክቱ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



