የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እያስመረቃቸው ያሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥኑ እና የተቋሙን የላቀ አፈጻጸም የሚያሳዩ የድል ማህተሞች መሆናቸውን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገለፁ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምርቃት ላይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ከተለያዩ የኃይል አማራጮች ከ160 ጊጋ ዋት በላይ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል እምቅ አቅም አለ።

ተቋሙ ይህን እምቅ አቅም በመጠቀም እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት በአስተማማኝ መልኩ ለመመለስ ትውልድን ታሳቢ ያደረጉ ዘመን ተሻጋሪ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እየገነባ ይገኛል ብለዋል።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ጨምሮ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተቋሙ ሦስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ማስመረቁን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቁመዋል።
የተመረቁት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥኑና የተቋሙን የላቀ አፈጻጸም የሚያሳዩ የድል ማህተሞች ሲሉ ገልፀዋቸዋል።፡
የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ መግባታቸው ሀገራዊ የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን፣ ግብርናን ለማዘመን እና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት እንዲሁም የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ግብ በማሳካት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ኢንጅነር አሸብር አብራርተዋል።
ከ145 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በሆነ ወጭ የተገነባው የአሰላ የኃይል ማመንጫ በ29 የንፋስ ተርባይኖች 100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለው ጠቁመዋል።
ይህም እንደሀገር ከንፋስ የሚመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል 504 ሜጋ ዋት ከማድረሱም ባለፈ ተቋሙ የኃይል ስብጥሩን ለማመጣጠን የሰጠውን ትኩረት ማሳያ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለጻ ፕሮጀክቱ በተርባይኖች የማመንጨት አቅም፣ በማማው ቁመት እና በክንፎቹ ርዝመት እስከአሁን በሀገራችን ከተገነቡ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ልዩ ያደርገዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ከውሃ ኃይል ማመንጫዎች ጋር ተደማሪ ሆኖ በመሥራት በበጋና በድርቅ ወቅት በግድቦች ውሃ መቀነስ ምክንያት የሚፈጠርን የኃይል እጥረት በመቅረፍ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ የተመረቁ ፕሮጀክቶች በጥራት ተጠናቀው ወደ አገልግሎች እንዲገቡ መንግሥት ያደረገው ድጋፍ እና የሰጠው አመራር የኃይል ተደራሽትን ለማሳደግ እና እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ አቅም መፍጠሩንም ኢንጂነር አሸብር አስታውቀዋል ።



የተቋሙ የፕሮጀክት አመራር ብቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻሻል መንግሥት እያደረገ ያለው ድጋፍ በቀጣይ የሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመፈፀም አቅም እንደሚሆንም ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ያደረገው የዕዳ ሽግሽግ የተቋሙ የፋይናንስ አቅምና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን አስታውሰዋል።
ይህም ለፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ገንዘብ በራሱ ፋይናንስ ጭምር እንዲሸፍን በማስቻል የተቋሙ የመፈፀም አቅም እንዲሻሻል አድርጓል ነው ያሉት።
በዘርፉ የሚታዩ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ውስንነቶችን በመቅረፍ ሁሉንም የኃይል ምንጭ ሀብቶች ጥቅም ላይ ለማዋልና የኃይል ስብጥሩን ለማሳደግ በመንግሥትና የግል አጋርነት የሚለሙ ፕሮጀክቶች ተለይተው ወደ ሥራ መገባቱን በመጥቀስ የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለውጤት እንዲበቃ በተለያየ መልኩ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

