መንግሥት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያከናወነው የለውጥ ሥራ ውጤት እንደተገኘበት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምረቃ ላይ እንደተናገሩት አርሲ በስንዴና ገብስ ምርት ብቻ ሳይሆን በኢነርጅ ዘርፍም ከፍተኛ አቅም አለው።
በአካባቢው ከአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ በተጨማሪ ሁለት የከርሰ ምድር እንፋሎት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ 4 ሺህ ሜጋ ዋት አካባቢ የነበረው ኃይል የማመንጨት አቅም አሁን ላይ ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት መጠጋቱን እንዲሁም 7 ቢሊዮን ብር የነበረው የተቋሙ ዓመታዊ ገቢ ከ75 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
ተቋሙ ለዘመናት በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ የነበረ በመሆኑ በፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ላይ ችግሮች ነበሩበት ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ይሁንና መንግሥት በተቋሙ ላይ ያከናወነው የለውጥ ሥራ አበረታች ውጤት እየተገኘበት ስለመሆኑም ገልፀዋል።
በተከናወነው የለውጥ ሥራ ተቋሙ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፉት ስድስት ወራት የ7 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውሰዋል።

ያለፉት የለውጥ ዓመታት ፕሮጀክት መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ፤ መክሰር ብቻ ሳይሆን ማትረፍ የተለማማድንበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንዲጠናቀቁ በተከናወነው ሥራ ባለፉት አምስት ዓመታት አራት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን መጠናቀቃቸውን አስረድተዋል።
የአሰላ የንፍስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 145 ሚሊዮን ዩሮ ወጭ ቢደረግበትም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወጭውን በመመለስ ትርፍ ማስገኘት የሚችል በመሆኑ ቀጣዩ ትውልድ ትርፍን እንጅ ዕዳን የሚረከብበት ሁኔታ እንዳይኖር እንደሚያግዝ አንስተዋል።

የዴንማርክ መንግስት ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በዝቅተኛ ወለድ የረጅም ጊዜ ብድርና ድጋፍ በመስጠት አርዓያ የሚሆን ሥራ በመስራቱ የኢትዮጵያ መንግስት ፕሮጀክቱን ከደንማርክ መንግስት እንደተበረከተ ስጦታ ይቆጥረዋል ነው ያሉት።
በፕሮጀክቱ አካባቢ የተሰራው የ27 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን ወደ ማዕከላዊ ገበያ ተደራሽ እንዲያደርጉ እንደሚያግዛቸው ም ጠቅሰዋል።
በኢነርጂ ዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሻሉ እና የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያረጋግጡ ናቸው ያሉት ዐቢይ በቀጣይ የህዝባችን ሕይወት እስኪለወጥ ድረስ የጀመርነውን ልማት ተግተንን እንሰራለንም ብለዋል:




በፕሮጀክቱ የምረቃ ሥነ -ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር)ጨምሮ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ በኢትዮጵያ የደንማርክ አምባሳደር፣ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።



