ተቋሙ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን የኃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

ተቋሙ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን የኃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን የኃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ ገለፁ፡፡

ከጋና የመጡ ባለሙያዎች ተቋሙ በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች የኃይል አቅርቦት ዙሪያ እያከናወናቸው ባሉ ሥራዎች ዙሪያ በተዘጋጀው የልምድ ልውውጥ መድረክ ላይ ተወካይ ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነር ያለውአይቀር ማንደፍሮ እንደገለጹት እንደ ሀገር እ.ኤ.አ እስከ 2029 የሚቆይ የብሔራዊ የኤሌክትሪክ መኪኖች ትግበራ ስትራቴጅ ተቀርጾ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ለኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሀገራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ሆኖ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ የአፍሪክ የታዳሽ ኃይል ማዕከል የመሆን ርዕይ ሰንቆ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ያሉት አቶ ያለውአይቀር ኢትዮጵያ አሁን ላይ 100 ሺህ የሚደርሱ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ወደ ሥራ በማስገባት ከአፍሪክ ቀዳሚ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ በስትራቴጅክ ዕቅዱ ላይ በተቀመጠው መሠረት በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ሊኖሩ የሚችሉ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ታሳቢ በማድረግ በግሪድና በኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተጽዕኖ በተመለከተ የባለሙያዎች ቡድን አዋቅሮ ጥናት ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡

የኢነርጅ ሴኪዩሪቲ ከኃይል አቅርቦት በተሻገረ የሀገር ደህንነት መሆኑን ያነሱት ተወካይ ሥራ አስፈጻሚው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ፈጣን ቻርጀሮች በግሪዱ እና በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ በጥናት ላይ የተመሰረቱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ይዘንጋው ይታይህ የትራንስፖርት ዘርፉ ከአየር ብክለት የጸዳ እና የዘመነ እንዲሆን እንደ ሀገር የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በስፋት ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በ2030 ላይ 500 ሺህ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን እና 2 ሺህ 230 የቻርጅ ማዕከላት እንዲኖሩ በስትራቴጅው በዕቅድ ተይዞ እየተሰራበት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ይህም በዓመት ለነዳጅ የሚወጣውን ከ5 እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እና ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን የበካይ ጋዝ ልቀት በ13 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ለመቀነስ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የጋና ልዑካን ቡድን አባልና በጋና ፐብሊክ ዩቲሊቲ ሪጉላቶሪ ኮሚሽን ሪጅናል ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ሚስተር አልሃጂ አቡካሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪክ በኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ አተገባበር ላይ የተሻለች በመሆኗ እስከ አሁን ከመጣችበትና እየተገበረቻቸው ካሉ አሰራሮች ልምድ ለመውሰድ እና በዘርፉ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡

በኤሌክትሪክ መኪኖች ላይ ባለድርሻ የሆኑ የትራንስፖርትና የኃይል ዘርፎችን እንዲሁም ተቆጣጣሪ መ/ቤቶች ላይ የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውንና በቆይታቸው ተጨባጭ እውቀቶችንና ልምዶችን መቅሰማቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ትግበራ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከፍተኛ የመንግስት አካላት ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው ከፍተኛ ውጤት ሊመዘገብ መቻሉን እንደታዘቡም ጠቁመዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top