የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው የግል ባለሀብቱ በኃይል ልማት ዘርፉ እንዲሳተፍ በር ይከፍታል

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው የግል ባለሀብቱ በኃይል ልማት ዘርፉ እንዲሳተፍ በር ይከፍታል

በኢትዮጵያ በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው  የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ የግል አልሚዎች በኃይል ልማት ዘርፍ እንዲሳተፉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ።

ሥራ አስፈፃሚው አቶ ውድነህ የማነ እንዳስታወቁት በሀገሪቱ የነበሩ የህግ ማዕቀፎች፣ የውጭ ምንዛሪ  ችግሮች እና ሌሎች አሰራሮች የግል አልሚዎች በዘርፉ እንዳይሳተፉ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የግል ባለሃብቱ በኃይል ልማት እንዲሳተፍ የሚጋብዝ የህግ ማዕቀፍ ቢዘጋጅም አልሚዎችን የሚያበረታታ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ባለመኖሩ ወደተግባር ሳይገባ እንደቆየ አቶ ውድነህ አስረድተዋል።

አሁን በሀገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው  የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ላይ እንዲሳተፉ የሚያበረታታ እንደሆነ አቶ ውድነህ አመልክተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው በሀገሪቱ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት የሀገር ውስጥ የኃይል አቅርቦት ጥያቄን ለመመለስ እና የኃይል  ኤክስፖርት ተደራሽነትን ለማስፋት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው  አስገንዝበዋል፡፡

ኃይል ማመንጨት ብቻውን ግብ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ውድነህ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው የልማት ሥራዎችን መደገፍ ሲችልና በሀገሪቱ የማኑፋክቸሪንግ እና የኢንዱስትሪ ልማቶችን ሲያሳድግ ነው ብለዋል።

በግሉ ዘርፍ ሊለሙ የሚችሉ የኃይል መሠረተ ልማቶች ተለይተው የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የጠቆሙት ሥራ አስፈፃሚው በቅርቡ በግል አልሚ እንዲለማ የተፈረመው የአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በማሳያነት አንስተዋል።

በቀጣይም የግል ባለሃብቶች መሠረተ ልማቱን ሊደግፉ የሚችሉባቸው ዘርፎች እየተለዩ ተግባራዊ እንደሚደረጉ አመልክተዋል።

የግል ባለሃብቱም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በኃይል መሠረተ ልማቱ ላይ ኢንቨስት በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚን መደገፍ እንደሚጠበቅበት አቶ ውድነህ ጥሪ አቅርበዋል።

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top