ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ26 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የፋይናንስ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደመረ አሰፋ እንደገለፁት ገቢው የተሰበሰበው ከኃይል ሽያጭ፣ ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ እና ከባለፈው ዓመት ከዞረ የኃይል ሽያጭ እንዲሁም ከልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች ነው፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 27 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ከ26 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የዕቅዱን 96 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡

ገቢው የተገኘው ለሀገር ውስጥ ከቀረበ የኃይል ሽያጭና ከኦፕቲካል ፋይበር ኪራይ 19 ነጥብ 59 ቢሊዮን ብር፣ ለውጭ ሀገር ከቀረበ የኃይል ሽያጭ 5 ነጥብ 88 ቢሊዮን ብር፣ ለዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች ከቀረበ ኃይል 945 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር እና ቀሪው ከተለያዩ የገቢ ምንጮች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት የሰበሰበው ገቢ ካለፈው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 19 ነጥብ 8 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማጠናከር፣ ወቅቱን የጠበቀ ክትትል በማድረግ እና የኃይል ሽያጩን ከሚያከናውነው የማርኬቲንግ ክፍል እንዲሁም ከደንበኞች ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ በመሰራቱ በገቢ አሰባሰብ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመደበኛ ወጪዎች እንኳ ከራሱ ገቢ ሰብስቦ መሸፈን አይችልም ነበር ያሉት አቶ ደመረ አሁን ላይ ግን የገቢ አሰባሰቡን በማዘመንና በማጠናከር መደበኛ ወጪውን ሸፍኖ በራሱ ገቢ የካፒታል ፕሮጀክቶቹን ለመሸፈን ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

በቀጣይ የተቋሙን የገቢ አማራጮችን በማስፋትና ወጪ በመቀነስ ብሎም ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጎልበት የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ደመረ አብራርተዋል፡፡

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top