የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማከፋፈያ ጣቢያዎችን የኃይል ጭነት ለማቃለል የ38 አዳዲስ ትራንስፎርመሮችን ግዥ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን የሪጅኖች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ወልደማርያም እንዳስታወቁት ተቋሙ ከ50 እስከ 250 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮችን በሦስት ዙር ለመግዛት በሂደት ላይ ነው፡፡
ትራንስፎርመሮቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ጭነት በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡


ከታቀዱት 38 ትራንስፎርመሮች መካከል የመጀመሪያው ዙር የ9 ትራንስፎርመሮች የግዢ ሂደት ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት በምርት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስምንት ባለ 230 እና 132 ኪሎ ቮልት የጂ.አይ.ኤስ (GIS) የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለመጠገን የሚያስችል የባለሙያዎች ሥልጠና ለመስጠት ዕቅድ መያዙንም ገልፀዋል፡፡
ከስምንቱ የጂ.አይ.ኤስ (GIS) ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ አራቱ ለከተማዋ የቀላል ባቡር ትራንስፖርት እንዲሁም ቀሪዎቹ ደግሞ ለነዋሪው ማህበረሰብ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በመስጠት ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡
ሥልጠናው በከፍተኛ ቮልቴጅ ጂ.አይ.ኤስ እና ትራንስፎርመር ጥገና ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የገለፁት ዳይሬክተሩ ይህም ባለሙያዎቹ ያላቸውን የክህሎት ክፍተት በመሙላት ጣቢያዎቹን በራስ አቅም ለመጠገንና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡
የጂ.አይ.ኤስ (GIS) ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ለሁለት አስርት ዓመታት ያለምንም ጥገና አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳላቸው የጠቀሱት አቶ ወንድወሰን በከተማዋ የሚገኙት እነዚህ ጣቢያዎች ላለፉት አስር ዓመታት የከፋ የጥገና ችግር እንዳላጋጠማቸውም ገልፀዋል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ካላቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አንፃር ለረጅም ጊዜ ጥገና የማይፈልጉና አነስተኛ ቦታ ላይ የሚገነቡ በመሆናቸው ለከተማዋ የኃይል አቅርቦት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ወደፊት ችግሮች ቢከሰቱ በራስ አቅም ለመጠገን እንዲቻል ባለሙያዎችን ለማብቃትና ለጣቢያዎቹ የሚያስፈልጉ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለማሟላት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

