ባለፉት 3 ዓመታት በ60 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የብሬከር ማዘመን ሥራ ተከናውኗል

ባለፉት 3 ዓመታት በ60 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የብሬከር ማዘመን ሥራ ተከናውኗል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት 3 ዓመታት በ60 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የመቆጣጠሪያ ሥርዓት ወይም የብሬከር ማዘመን ሥራ ማከናወኑን በተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ወልደማርያም እንደገለፁት ከ2016 እስከ 2018 በጀት ዓመት ድረስ በ75 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የመቆጣጠሪያ ብሬከር ለማዘመን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡

ባለፉት 3 ዓመታት በ60 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የዘመናዊ መቆጣጠሪያ ብሬከር ገጠማ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በ13 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚከናወኑ የማዘመን ሥራዎችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ነው ዳይሬክተሩ ጠቆሙት።

እንደ አቶ ወንድወሰን ገለፃ ተቋሙ ወደ ዘመናዊ የጂ.አይ.ኤስ ቴክኖሎጂ መሸጋገር ያስፈለገው በዘይት በሚሰሩ ነባር ብሬከሮች ምክንያት የሚከሰቱ የኃይል መቆራረጦችንና የደህንነት ስጋቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሁም በማከፋፈያ ጣቢያዎች ያለውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በማዘመን የዲጂታል ቁጥጥር ሥራዎችን ለማከናወን ነው።

 ቀደም ሲል የነበሩት ብሬከሮች ይሸከሙት የነበረው 5 ሜጋ ዋት አቅም አሁን ላይ ከ 10 እስከ 20 ሜጋ ዋት እንዲያድግ መደረጉን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ይህም ለደንበኞች የሚቀርበውን የኃይል መጠን በእጥፍ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የተከናወነው የማዘመን ሥራዎች የብልሽት ድግግሞሽን በመቀነስ የኃይል መቋረጥ ርዝማኔን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳጠር ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን በጣቢያዎች የሚገኙ የባትሪዎችን ደህንነት በየጊዜው ከመከታተል በተጨማሪ አገልግሎት የጨረሱና ብልሽት ያለባቸውን የባትሪ ሴሎችና ቻርጀሮችን በአዲስ የመተካት ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት 51 የባትሪ ቻርጀሮች እና 3 ሺህ 22 ነጠላ የባትሪ ሴሎችን በመቀየር የጣቢያዎችን የመከላከያ ሥርዓት ይበልጥ ውጤታማና አስተማማኝ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በቀጣዩ በጀት ዓመት የብሬከር ማዘመን ሥራ የሚያስፈልጋቸው ተጨማሪ 20 ማከፋፈያ ጣቢያዎች በጥናት ተለይተው ለሥራው የሚያስፈልጉ የቁሳቁስ ግዥ ሂደቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

Scroll to Top