የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ከ65 መቶ በላይ ተጠናቋል

የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ከ65 መቶ በላይ ተጠናቋል

የሺግዳን ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ አፈፃፀም ከ65 በመቶ በላይ መድረሱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የሳይት 2 ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ አርጋው ታዲ እንዳስታወቁት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የሲቪል ሥራ 70 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራ 35 በመቶ ተጠናቋል።

በአሁኑ ወቅት የአምስት ትራንስፎርመሮች እና የሁለት ሻንት ሪአክተሮችን ተከላ በማጠናቀቅ ዘይት የመሙላት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አርጋው ገለፃ የኦፕሬተሮች መኖሪያ እና የመቆጣጠሪያ ቤቶች ግንባታ መጠናቀቃቸውን ገልፀው በተጓዳኝ የጣቢያውን የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ እና ጠጠር የማልበስ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

የባዝባር ተከላ፣ የመቆጣጠሪያ እና ለኃይል ማስተላለፍ የሚያገለግሉ የመሬት ውስጥ ገመድ ዝርጋታዎች በቀጣይ የሚከናወኑ ቀሪ የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎች መሆናቸውንም ነው ያስረዱት፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ማከፋፈያ ጣቢያው 400 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው አምስት ትራንስፎርመሮች እና ሁለት ሻንት ሪአክተሮች እንዲሁም አንድ ባለ 132 እና አስራ አምስት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡

በፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ተቆጣጣሪ አቶ ተሻለ ታደሰ እንደተናገሩት ሥራ ተቋራጩ በዲዛይኑ መሰረት ግንባታዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያውን ቀሪ የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በፕሮጀክቱ የሀዮሰንግ ሄቪ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ሳይት መሃንዲስ አቶ ሚልኪ ጎሹ በበኩላቸው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው የግንባታ አፈፃፀም በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብና ጥራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጣቢያው ከኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ተረፈ ምርት የሚገኘውን ኃይል ወደ ብሔራዊ ቋት ለማስገባትና ለአካባቢው ማህበረሰብም ያልተቆራረጠና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

የሺግዳን ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ከ27 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወነ ሲሆን የግንባታና የማማከር ሥራው የኮሪያ ሪፐብሊክ ኩባንያ በሆኑት በሀዮሰንግ ሄቪ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን እና በባዮክሰን ፓወር አማካኝነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

Scroll to Top