የወይናንታ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ የሲቪል ሥራ ከ71 በመቶ በላይ መድረሱን የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራዎች አስተባባሪ አስታወቁ፡፡
አስተባባሪው አቶ ኤሊያስ መሀመድ እንደገለፁት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ያስችላል።
ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ኃይል ለማቅረብ ከአራት ዓመት በፊት ሥምምነት ቢፈረምም በወቅቱ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ግንባታው መዘግየቱን ገልፀዋል።
የማከፋፈያ ጣቢያው የስዊች ያርድ የሲቪል ግንባታ መጠናቀቁን ተከትሎ ትራንስፎርመሮችን የማስቀመጥ ሥራ መከናወኑን አቶ ኤሊያስ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የመቆጣጠሪያ ክፍሎች እና የመኖሪያ ቤቶች የማጠናቀቂያ ሥራዎች እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው ያብራሩት፡፡
የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በሙሉ ወደ ሳይቱ መድረሳቸውን የገለፁት አስተባባሪው በቀጣይ የኬብል ዝርጋታና የመቆጣጠሪያ ክፍል ሥራዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።
እንደ አቶ ኤሊያስ ገለፃ ጣቢያውን ከይርጋለም ቁጥር 2 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ጋር ለማገናኘት የሚያስፈልጉ የ25 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ተከላ ለማከናወን የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
ለማከፋፈያ ጣቢያው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያቀርበው የ132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አማካይነት እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው የገለፁት።



በሲኖ ሃይድሮ ኩባንያ የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ባህትዮ ኩምሳ በበኩላቸው ጣቢያው እያንዳንዳቸው 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች አሉት።
የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ ቢሆኑም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ በበልግ ዝናብ ምክንያት መጠነኛ መዘግየት እንዳጋጠመው ተናግረዋል፡፡

