የደቡባዊ የኤሌክትሪክ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የቲርጋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የሲቪል ሥራ አፈፃፀም 45 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራዎች ተቆጣጣሪ አስታወቁ።
ተቆጣጣሪው አቶ ደረጄ ክፍሌ እንደተናገሩት የመቆጣጠሪያ ክፍሉ የብረትና የኤሌክትሪክ ሥራዎች ተጠናቅቀው በአሁኑ ወቅት የጣሪያ ኮንክሪት ለመሙላት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በተጨማሪም የውስጥ ለውስጥ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች እና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በተጓዳኝ እየተከናወኑ መሆኑ ነው የተናገሩት፡፡
የፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች 15 በመቶ መድረሳቸውን የጠቀሱት አቶ ደረጄ ለተከላው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ወደ ፕሮክቱ ሥፍራ መድረሳቸውን አብራርተዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ትራንስፎርመሩን ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ የዘይት መሙላትና የማጣራት ሥራ እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡

ጣቢያው አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ጥምር ገቢ መስመር፣ አንድ ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር ትራንስፎርመር እና አምስት ባለ 33 ኪሎ ኪሎ ወጪ መስመሮች እንደሚኖሩት ነው የተናገሩት፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት፣ በዙሪያው ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና በግንባታ ላይ ለሚገኘው የስኳር ፋብሪካ ኃይል ለማቅረብ እንዲሁም ከፋብሪካው ተረፈ ምርት የሚመነጨውን ኃይል ወደ ብሔራዊ ግሪድ ለማስገባት ያስችላል።
እንደ ተቆጣጣሪው ገለፃ የግንባታ ግብዓቶች በቅርበት አለመገኘት፣ የነዳጅ እጥረት እና በአካባቢው ያለው አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ሥራዎችን በታቀደው መርሃ-ግብር መሠረት ለማከናወን አላስቻለም፡፡ የቲርጋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ኃይል ማከፋፈያ ጣቢ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ በ1 ሺህ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ ላይ እየተገነባ ይገኛል፡፡

