ኢትዮጵያን “የአፍሪካ የኃይል ማማ” የማድረግ ስልታዊ ራዕይ በምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት (EAPP) ውስጥ ባላት መሪነት በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል።
ሀገራችን ባላት ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና በተፈጥሮ በበለፀገ ሀብቷ ለምስራቅ አፍሪካ እንደ ቀጣናዊ ትስስር እንደ “ሞተር” ሆና እያገለገለች ነው።
የዚህ ታላቅ ስኬት ማሳያ የ “ምስራቅ ኤሌክትሪክ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር” (Eastern Electricity Highway Project) ነው።
የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን በቁጥር
- የኢትዮጵያን ወላይታ ሶዶ ከኬንያው ሱስዋ የሚያገናኝ 1,045 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ባለሁለት ዋልታ (Bipolar) 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የቀጥተኛ ቮልቴጅ (HVDC) መስመር ነው።
- በ1.26 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተጠናቀቀው ይህ መስመር እስከ 2,000 ሜጋ ዋት ኃይል የማስተላለፍ አቅም አለው።
- ኬንያ ከውጭ ሀገራት ከምታስገባው ኤሌክትሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ 83 በመቶውን በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም ኬንያ በሀገር ውስጥ ከእንፋሎት (Thermal) የምታመነጨውን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ኃይል በዝቅተኛ ወጪ እንድትተካ አግዟታል።
- ኬንያ ከኢትዮጵያ ለምትገዛው ኃይል በኪሎ ዋት ሰዓት (kWh) 6.5 ሳንቲም የምትከፍል ሲሆን ይህም በሀገር ውስጥ ለማምረት ከምታወጣው 9.4 ሳንቲም እጅግ ያነሰ በመሆኑ የካርቦን ልቀትን ለመግታትና ወጪን ለመቀነስ ያለውን ፋይዳ ያሳያል።
የቀጣናዊ ትስስሩ አድማስ
- ከኬንያ ባለፈ ለጅቡቲና ለሱዳን ከተላከው የኤሌክትሪክ ኃይል በ2017 በጀት ዓመት ወደ 118 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።
- ወደ ታንዛኒያ የኃይል ሽያጭ በመጀመሩ ተጨማሪ ገቢ እየተገኘ ሲሆን ከደቡብ ሱዳንና ከሶማሊያ ጋር የኃይል ትስስር ለመጀመር የአዋጭነት ጥናቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
ይህ የኃይል ትስስር መረብ ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘቱም በላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንደገለጹት በአፍሪካ ቀንድ “የጋራ ሀብትና የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ” እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል።