የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን የኃይል አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው የወይናንታ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ የጀመሩ ፋብሪካዎችን የኃይል ጥያቄ እንደሚመልስ የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ባዴጎ በቀለ እንደገለፁት የወይናናታ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ከ50 ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ያቀርባል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ፓርኩ ምርታቸውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰሩ ለሚገኙ ዘጠኝ ፋብሪካዎች እያቀረበ ያለው የኃይል መጠን 12 ሜጋ ዋት ብቻ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በመሆኑም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ ከፍላጎቱ ጋር አለመመጣጠኑ የፋብሪካዎቹን የማምረት አቅም ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ አቶ ባዴጎ ጠቁመዋል፡፡


በፓርኩ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች መኖራቸውን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ወደፊት በዕቅድ የተያዙ 34 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ሲገቡ የኃይል ፍላጎቱ ከማከፋፈያ ጣቢያው አቅም በላይ ሊሆን እንደሚችልም አብራርተዋል፡፡
ስለዚህም የፓርኩን የወደፊት 150 የኢንዱስትሪ ሼዶች የኤሌክትሪክ ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ ተጨማሪ የማስፋፊያ ግንባታዎችና የኃይል ማሻሻያ ሥራዎች በወቅቱ መከናወን እንዳለባቸውም ነው የጠየቁት።
የወይናናታ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት መጠናቀቅ አስተማማኝና ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ ከማገዙም ባሻገር በኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት ያልቻሉ ፋብሪካዎች በቀጥታ ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የገለፁት፡፡
ይህም ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደ ፓርኩ ለመሳብ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ባዴጎ ገለፃ የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ በፓርኩ ውስጥ በቀን ከ4 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የቆሸሸ ውሃ ለማጣራት ታቅዶ እየተገነባ ለሚገኘው ግዙፍ የቆሻሻ ውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብም ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡

