የማከፋፈያ ጣቢያውን ግንባታ እስከ መጪው ሐምሌ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

የማከፋፈያ ጣቢያውን ግንባታ እስከ መጪው ሐምሌ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታን እስከ መጪው ሐምሌ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡
 
ሥራ አስኪያጁ አቶ ቴዎድሮስ ጋሻው እንደገለጹት የማከፋፈያ ጣቢያው ከቆቃ-ገላን ከተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ላይ በመቀጠል 14 ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እና እያንዳንዳቸው ባለ 63 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው አራት ትራንስፎርመሮች እንዲኖሩት ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያውን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ለማስቀመጥ የሚያግዙ ከ290 በላይ የመሠረት ቁፋሮና የኮንክሪት ሙሌት እንዲሁም የአራት ትራንስፎርመሮች ማስቀመጫ ግንባታዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የሲቪል ሥራዎች ስለተጠናቀቁ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች በመርሀ ግብሩ መሰረት ሳይት ከደረሱ ቀሪ የተከላ ሥራዎች በተያዘው እቅድ መሰረት እንደሚከናወን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የኦፕሬተሮች መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻፀም 48 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን የጠቆሙት አቶ ቴዎድሮስ ቀሪ የመንገድ፣ የመቆጣጠሪያ ክፍሉ ግንባታ እና የፍሳሽ ማስወገጃ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሚካኒካል ሥራዎችን የማካካሻ እቅድ በማውጣት ፕሮጀክቱን እስከ መጭው ሐምሌ 2017 ዓ.ም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ባለስልጣን ለሚያስገነባው ስማርት ሲቲ በተለያዩ ምዕራፎች እንዲቀርብለት ከሚፈልገው 575 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል ውስጥ ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ 252 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያውን ጨምሮ 2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላለው የማስተላለፊያ መስመር የግንባታ ሥራ የሚያስፈልገው ወጪ በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለስልጣን እየተሸፈነ ነው።

ፕሮጀክቱ ለ181 ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድሎች ፈጥሯል፡፡


? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top