በሻሸመኔ ባለ 132/33/15 ኪሎ ቮልት ማከፋፊያ ጣቢያ ረጅም ዓመት ያገለገሉ መቆጣጠሪያዎችን በዘመናዊ የጂ አይ ኤስ መቆጣጠሪያዎች የማዘመን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ምሕረቱ ግዛው እንደገለጹት ጣቢያው ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ መቆጣጠሪያዎችን በዘመናዊ የጂ አይ ኤስ ብሬከሮች በመቀየር የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ እየተሰራ ነው።

ማከፋፈያ ጣቢያው ካለው 60 ሜጋ ዋት የመጫን አቅም በአሁኑ ወቅት 50 ሜጋ ዋት እየጫነ መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ በጣቢያው የተጀመረው የ15 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያዎችን የማዘመን ሥራም ወደመጠናቀቁ ተቃርቧል ብለዋል።
የጣቢያ የኦፕሬሽን ሰራተኛ አቶ ሰጠኝ ተስፋዬ በበኩላቸው የቆዩ መቆጣጠሪያዎችን ዘመኑ በደረሰበት የመቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ መቀየራቸው ከኃይል መቋረጥ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ችግሮችን እንደሚፈታ ተናግረዋል።

መቆጣጠሪያዎችን የማዘመንና የመቀየር ሥራው በተቋሙ ሠራተኞች መከናወኑ የሠራተኞችን ክህሎትና ዕውቀት በማሳደግና ወጪን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልፀዋል።
የሻሸመኔ ማከፋፈያ ጣቢያ 50 እና 25 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው ሁለት ፓወር ትራንስፎርመሮች፣ አራት ገቢ መስመሮች እንዲሁም ዘጠኝ ባለ 15 እና ሦስት ባለ 33 ወጭ መስመሮች አሉት፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው ለመቱ፣ ለዋርካ፣ ለሮጲ፣ ለወንዶ ገነት፣ ለአርሲ ነገሌ፣ ለኮፈሌ ፣ ለሻሸመኔ ከተማ እና አካባቢዉ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እየሰጠ ይገኛል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”






