የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የሚያልፉበትን ቦታ በዘመናዊ ሶፍትዌር ታግዞ ለመምረጥ የሚያስችል ስልጠና መሰጠቱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ፡፡
በዘርፉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዲዛይን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው ፀጋ እንዳስታወቁት ስልጠናው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አርክ ጂአይ ኤስ በተሰኘ ሶፍርዌር በመታገዝ የተሰጠው ለ30 የዲዛይንና የቅየሳ ባለሙያዎች ነው፡፡



በሁለት ዙር የተሰጠው ስልጠና መስመሮቹ ከመገንባታቸው በፊት የሚያልፍበትን አካባቢ በሶፍትዌር በመታገዝ ለመምረጥ እና ሥራውን በቀላሉ ለማከናወን የሚያስችል ብቃት ያለው ባለሙያ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በፊት የዲዛይን ስራው የማስተላለፊያ መስመሮች የሚያልፉበት ቦታ በእግር በመሄድና ጎግል ኤርዝና ጎግል ማፕ የመሳሰሉ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም ሲከናወን እንደነበር አስታውሰው አዋጭ የሆነ መስመር ከመምረጥ አንፃር ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በሶፍትዌሩ በመታገዝ መስመሩ የሚያልፍበትን አካባቢ በመምረጥና በሶፍትዌር የተገኘውን ኮርዲኔት መሰረት በማድረግ ወደ ቦታው በመሄድ ከአካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ እና በዋጋ አዋጭ የሆነ የማስተላለፊያ መስመር ዲዛይን ለማዘጋጀት እንደሚያስችል አቶ ዳኛቸው አስረድተዋል፡፡
የመስተዳድር አካላት የጂአይኤስ ሶፍትዌር የሚጠቀሙ በመሆናቸው ተቋሙ የሚጠየቀውን መረጃዎች ለማቅረብ ችግሮች ያጋጥሙት እንደነበር ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል።


ሶፍትዌሩ ከመስተዳድር አካላት ጋር ተመሳሳይ የሆነ መረጃ ለመለዋወጥ ከማስቻሉም በላይ ከመስተዳድሮች፣ ከአማካሪዎች፣ ከአበዳሪ ተቋማት እና ከሥራ ተቋራጮች ጋር በዘመናዊ ሶፍትዌር በመግባባት የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
በተቋሙ እየመጡ ያሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ታሳቢ በማድረግ በቀጣይ አርክ ጂአይኤስን ጨምሮ በሌሎች የተለያዩ ሶፍትዌሮች ላይ ለባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ስልጠናውን ከወሰዱት መካከል የማስተላለፊያ መስመር ዲዛይን ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ከቤ ታምሩ በበኩላቸው ከስልጠናው በቀጣይ ለሚያከናውኑት ሥራ ግብዓት የሚሆን ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል መስመሮች የሚያልፉበትን አካባቢ በእግር በመሄድ ሲመረጥ እንደነበርና በዚህም ሠራተኛው ለከፍተኛ እንግልት ይዳረግ እንደነበር ገልፀው ሶፍትዌሩ የባለሙያዎችን ድካም ባቀለለ መልኩ መስመሮቹ የሚያልፉበትን አካባቢ ቢሮ ሆኖ ለመምረጥ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም ሶፍት ዌሩ መስመሮች የሚያልፉበትን አካባቢ ከወንዝ፣ ከደን፣ ከከተማ፣ ከመንገድ፣ ከማመንጫ እና ከማከፋፈያ ጣቢያዎች ያላቸውን ርቀት በመየት አዋጭ መስመር ለመምረጥ ያስችላል ብለዋል፡፡
ሶፍትዌሩ የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች የሚተከሉበትን ቦታ እንደሚያመላክትና ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን የዋጋ ትንተና ሥራ እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

