በማከፋፈያ ጣቢያዎች በተከናወኑ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ከ400 ሜጋ ዋት በላይ ተጨማሪ ኃይል ማግኘት ተችሏል

በማከፋፈያ ጣቢያዎች በተከናወኑ የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ከ400 ሜጋ ዋት በላይ ተጨማሪ ኃይል ማግኘት ተችሏል


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት 5 ዓመታት በ10 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ባከናወናቸው የትራንስፎርመር አቅም ማሳደግ ሥራዎች 439 ሜጋ ዋት ወይም 487 ነጥብ 3 ሜጋ ቮልት አምፒር ተጨማሪ ኃይል ማግኘቱን አስታወቀ።

በተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን የሪጅኖች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ወልደማርያም እንደገለፁት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማረጋገጥና እያደገ የመጣውን የደንበኞች የኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለመመለስ በትኩረት እየሰራ ነው።

ባለፉት 5 ዓመታት በለገጣፎ፣ ቦሌ ለሚ 2፣ አዳማ 2፣ ወልቂጤ፣ ሚዛን፣ ባህር ዳር፣ ኮምቦልቻ 2፣ ገፈርሳ፣ ባሌ ሮቤ እና አዲስ ዌስት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም ማሳደግ እና የተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተከላ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በአሁኑ ወቅት በቦሌ ለሚ ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ 56 ነጥብ 7 ሜጋ ዋት ለማግኘት የሚያስችል የ63 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር አቅም ማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው።

የአቅም ማሳደግና የማሻሻያ ሥራዎች የቴክኒክ ብልሽቶችን በመቀነስና የኃይል መቆራረጥን በማስወገድ ረገድ የታለመላቸውን ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውንም ነው የገለፁት።

ይህም ለደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራት ከማሳደጉም በላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተረጋጋና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲደገፍ የላቀ ሚና እንደሚጫወት ነው ያብራሩት፡፡

ይህ የአቅም ማሳደግና የማዘመን ተግባር በተቋሙ ባለሙያዎች የተከናወነ በመሆኑ ተቋሙ ለከፍተኛ ወጪ ሳይዳረግ የኃይል አቅርቦቱን ለማሻሻል ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ወንድወሰን ገለፃ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት የቴክኒክ ሥራዎች ተቋሙ በቀጣይ ለሚያጋጥሙ መሰል ተግዳሮቶች በራስ አቅም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን ከፍተኛ ልምድ የተገኘባቸው ናቸው።

Scroll to Top