በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጋራ በሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያ ዙሪያ ለሚገኙ 12 ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ የተከናወነው ሥራ የእኔነት ስሜት በመፍጠር የኃይል መሰረተ ልማት ጥበቃ ሥራዎችን እንደሚያጠናክር የወላይታ ሶዶ ኮንቨርተር ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ሀብታሙ ግርማ እንደገለፁት ጣቢያው ከተሰጠው ሀገራዊና ቀጣናዊ ተልዕኮ በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ተቋሙ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በቅንጅት በመስራት በጣቢያው ዙሪያ ለሚገኙ ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በማድረግ በማህበረሰቡ ሲነሳ የነበረውን የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎች መመለስ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
ተቋሙ ለአካባቢው ማህበረሰብ የኃይል ተደራሽ ለማድረግ የገባውን ቃል በተግባር አሳይቷል ያሉት ሥራ አስኪያጁ የተከናወነው ሥራ አሁን ተጠቃሚ ከሆኑት በተጨማሪ ከ22 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የወላይታ ሪጂን ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ መና በበኩላቸው 12 ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ 32 ትራንስፎርመሮችን የመትከል እና 143 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የማሰራጫ መስመሮችን የመዘርጋት እና 2 ሺህ 712 ቆጣሪዎችን የማገናኘት ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

በማህበራዊ ኃላፊነት ሥራ የተከናወነው የኃይል ተደራሽነት እንደ ሀገር የገጠር ኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማስፋት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚያግዝም አንስተዋል፡፡
የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራው የአካባቢው ማህበረሰብ ለኃይል መሰረተ ልማቶቹ በእኔነት ስሜት እያደረገ ያለውን ጥበቃ እንደሚያጠናክረውም የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡
የኃይል ተደራሽነቱ የአካባቢው ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ፣ በአካባቢው የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የማህበረሰቡን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ጤናው የተጠበቀ፣ በአስተሳሰብና በኢኮኖሚ የጎለበተ እንዲሁም ዘመናዊነትን የተላበሰ ማህበረሰብ በመፍጠር በኩል የራሱን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ለቀበሌዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ከተመደበው ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ውስጥ 60 በመቶው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተቀረው 40 በመቶ ደግሞ የተሸፈነ መሆኑ ተገልጿል፡፡


