የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመፍታት የእኔነት ስሜትን ለማሳደግ ይሰራል

የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመፍታት የእኔነት ስሜትን ለማሳደግ ይሰራል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከገናሌ ዳዋ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የካሳ ክፍያ እና የውሃ አቅርቦት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር ታህሳስ በትላንትናው ዕለት አካሂዷል።

በውይይቱ ላይ ከካሳ ክፍያ፣ ከጣቢያው የጥብቅ ወሰን (በፈር ዞን)፣ ከግድቡ የውሃ አለቃቀቅ እና የልማት ተነሺዎችን መልሶ ከማቋቋም እንዲሁም በኃይል ማመንጫው የውሃ መግቢያ (intake) አካባቢ ስለተገነባው የነገሌ ቦረና ከተማ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት በተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የአስተዳደራዊ ጉዳዮችና ዶክመንቴሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ  ታምሬ በተደጋጋሚ የሚነሱ የካሳ ጥያቄዎች ለተቋሙና ለጣቢያው የኦፕሬሽን ሥራ ፈተና ሆኖበታል፡፡

ተቋሙ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን እንደነበርም ያስታወሱት ሥራ አአስኪያጁ በፕሮጀክቱ ለልማት ተነሽዎቹ 3 ቢሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን ገልፀዋል።

ይሁንና በዚህ ሂደት ካሳ ያልተከፈለው የልማት ተነሺ ስለመኖሩ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ከቀረበ በህጋዊ አግባብ እንደሚስተናገድ አስታውቀዋል።

የነገሌ ቦረና ከተማ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ከግድቡ ጥብቅ ወሰን ውስጥ መሰራቱንና ይሄም ትክክል እንዳልነበር የጠቁሙት አቶ ዋለ ችግሩ በዘላቂነት በሚፈታበትና ማህበረሰቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በሚያገኝበት ዙሪያ ተቋሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ተቋሙ በጣቢያው ዙሪያ ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመፍታት በጣቢያው ላይ የእኔነት ስሜትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎችን እንደሚያከናውንም ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የልማት ተነሲዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ተስፋ በበኩላቸው የማመንጫ ጣቢያው የሀገር ብሔራዊ ኩራት ከሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ብለዋል።

ከጣቢያው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢነታቸውን ዳግም በመፈተሽና በማረጋገጥ ለቅሬታዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የልማት ተነሺዎች ችግር በተጋነነ የካሳ ክፍያ ብቻ የሚፈታ ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት መኖሩን የጠቆሙት አቶ አለማየሁ ካሳ እየተገባቸው ሳያገኙ የቀሩ ካሉ መረጃዎቻቸውን በማሰባሰብና በማረጋገጥ እንደሚፈታ ተናግረዋል።

ከውሃ አቅርቦት ጋር ያለው ችግር በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንዲሠራም ጠይቀዋል።

በውይይቱ የተነሱ ሀሳቦችን እንደግብዓት በመውሰድ ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት አመራሩ በትብብር መንፈስ ማህበረሰቡን ማዕከል አድርጎ መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በውይይቱ ላይ የክልሉ የልማት ተነሺ እና የውሃ ሀብት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዞንና የወረዳ መስተዳድር አካላት ተሳትፈዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top