የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ

የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በቅርቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ

የኢትዮጵያ የአንድነት ተምሳሌት የሆነውና ብዙ ውጣ ውረድ የታየበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በቅርቡ አገልግሎት እንደሚጀምር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በሚቀጥሉት 6 ወራት የግንባታውን ቀሪ ሥራዎች በማጠናቀቅ የፕሮጀክቱን ፍፃሜ ለኢትዮጵያ ህዝብ እናበስራለን ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካ ኩራት ከመሆኑም ባሻገር መቻልን ያሳየንበት፣ በውስጣችን ያለውን ውድቀት ያረምንበት እና 74 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ውሃ ይዘን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የምናመርትበት ሀብት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ የህዳሴ ግድብ አፍሪካውያን የፋይናንስና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ቢደረግባቸው እንኳ የራሳቸውን ሀብት በገዛ ዜጎቻቸው አልምተው መቀየር እንደሚችሉ በተግባር የሚያሳይ ነው፡፡

የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ስላለው ዲፕሎማሲ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት እንጂ ማንኛውንም ሀገር የመጉዳት ፍላጎት የላትም ብለዋል፡፡

ስለሆነም ግድቡ ግብፅን ጨምሮ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያመጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

ከግብፅ ጋር በተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በአስዋን ግድብ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ለውይይት፣ ለድርድር እና  በትብብር አብሮ ለመስራት ሁል ጊዜም በሯ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top