
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአንገት መድፋት ወደ ደረት መንፋት አሸጋግሮናል ሲሉ የአፍሪካ አመራት ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝደንት አቶ ዛዲግ አብርሃ ተናገሩ።
ፕሬዝደንቱ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራሮች በተቋሙ ዋና መ/ቤት የአመራርን ስልጠና ሲሰጡ እንደተናገሩት የህዳሴ ግድብ ከኃይል ማመንጫነት ባሻገር ለኢትዮጵያውያን ያለው ትርጉም የላቀ ነው።
“የህዳሴ ግድብ የሀገራዊ ትራንስፎርሜሽን የማዕዘን ድንጋይ ነው።” ያሉት አቶ ዛዲግ ግድቡ ለሀገር ከሚያስገኘው የኢኮኖሚ ጥቅም በላይ ለዓለም የከባቢ አየር ጥበቃ ድርሻው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።
የውሃ ኃይል ግድቦች በሩቅ ምስራቋ ቻይና በዓለም የመጀመሪያው ሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲጀመር መሰረት መሆናቸውን ጠቅሰው የሚመነጨው ኃይል ከኢኮኖሚ ጥቅም በላይ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።
አቶ ዛዲግ እንዳሉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የብሄራዊ ኩራት ምንጭ በመሆኑ ግድቡ ከታሪካዊ ማንነታችን ጋር በጥብቅ በተሳሰረው የአባይ ወንዝ ላይ መገንባታችን ኩራቱን ከፍ እንደሚያደርገው ገልፀዋል።
ግድቡ በሚያመነጨው ኃይል፣ በሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ እና በሚፈጥረው ትስስር ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት የወሳኝነት ሚና እንዲጎለብት የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአባይን ውሃ እንዳንጠቀም ብዙ ሴራ ቢሸረብብንም ያንን ሁሉ አልፈን የወሰንነው ውሳኔ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እርምጃ ነው ሲሉ የግድቡን የሉዐላዊነት መገለጫነት አስረድተዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያ ልማቷን ለማረጋገጥ የምትሄደውን ረዥም ርቀት ያሳየም ነው ብለዋል።
ስለትውልዳዊ ቅብብሎሽ ሲያነሱም “ጀምሮ ያለመጨረስ ታሪካችን የሁል ጊዜም አለመሆኑን በህዳሴው ግድብ አረጋግጠናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ ትውልድ ከአፄ ዳዊት ጀምሮ የነበረውን አባይን የመገደብ ህልም ከግብ ማድረስ የቻለ አኩሪ ትውልድ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዛዲግ “የቀደመውን ትውልድ ህልም ተቀብሎ እውን የማድረግ ተግባር አስቀጥለን ለትውልድ ማስተላለፍ ከቻልን ኢትዮጵያን ለሁልጊዜም የታላላቅ ጅምሮች እና የታላላቅ ፍጻሜዎች ሀገር እናደርጋታለን” ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በኤሌክትሪክ ኃይል በኩል ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም አውጥቶ መጠቀም እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዝደንቱ ይህንን ለማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ትልቁን ኃላፊነት እንደሚወስድ አስረድተዋል።
በመሆኑም የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ እያንዳንዱ ቤት የሚገባ በመሆኑ አፈጻጸሙ በሀገረ መንግስት ግንባታው ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
“የኤሌክትሪክ ኃይልን ተጠቃሚነት ማሳደግ ኢትዮጵያ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር ወሳኝ በመሆኑ ለኢኮኖሚያችን መዋቅራዊ ሽግግር መክፈቻ ቁልፉ መብራት ኃይል ጋር ነው ያለው ማለት ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ተቋሙ ወደ ውጪ ሀገራት በሚልከው ኢነርጂ ምክንያት የዲፕሎማሲ ሥራ እየሰራ ነው ሊባል እንደሚችል ጠቅሰዋል።
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

