በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጡ አገልግሎቶችንና አሰራሮችን ለማዘመን እየተከናወነ የሚገኘው የሳፕ ሲስተም ሁለተኛ ምዕራፍ ትግበራ አፈፃፀም 62 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱ ተገለፀ።
የተቋሙ ሥራ አመራር ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ሲስተሙን ከሚያለማው የህንዱ ኦሬን ኩባንያ ጋር በሳፕ የትግበራ አፈፃፀም ዙሪያ ግምገማ አካሂደዋል።
ግምገማው የመጀመሪያው ምዕራፍ የሳፕ ትግበራ ላይ የነበሩ ክፍተቶች የታረሙበትን ሁኔታ ለመረዳትና በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ የአሰራር ሥርዓቱ የደረሰበትን የትግበራ ደረጃ ለማወቅ ያለመ ነው።
በሁለተኛው የሳፕ ሲስተም የትግበራ ምዕራፍ የሚተገበሩ ሞጁሎችን አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሳፕ ትግበራ አማካሪና የኦሬን ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ማኑቺ ጉፕታ እንደተናገሩት በቀጣይ 3 ወራት ፕሮጀክቱን አጠናቆ ወደ ትግበራ ለማስገባት እየተሰራ ነው።
በሁለተኛው ምዕራፍ የሳፕ ትግበራ ላይ በሚካተቱት የፋይናንስ፣ ሰው ኃይል አስተዳደርና ግዥ እንዲሁም ዕቃ ግምጃ ቤት ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያም ለሥራ አመራሩ ሰጥተዋል።
በሲስተሙ ውስጥ አሪባ፣ ሰክሰስ ፋክተር፣ ፕላንት ሜንቴናንስ፣ ስፒር፣ ጂ.አር.ሲ የተሰኙ ሞጂሎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ የገለፁት ሚስተር ማኑቺ ሞጁሎቹ ሙሉ በሙሉ መተግበር ሲጀምሩ የተቋሙን የአሰራር ሥርዓት ለማዘመን ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል።
የፕሮሰስ ሞደርናይዜሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈለቀ አፈወርቅ በበኩላቸው በሁለተኛው ምዕራፍ የሳፕ ትግበራ አንዳንድ የሥራ ክፍሎች መረጃ በወቅቱ ባለመስጠታቸው በአሰራር ሥርዓቱ ትግበራ ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠሩን ጠቅሰው ፕሮጀክቱን በተያዘለት ዕቅድ ለማጠናቀቅ የሥራ ክፍሎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።
በግምገማው ወቅት የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ እንደገለፁት ተቋሙን ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥርዓት ለማሸጋገር እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን አድንቀዋል።
የአሰራር ሥርዓቱን ወደ ትግበራ ለማስገባት የቀረው ጊዜ አነስተኛ ቢሆንም ለፕሮጀክቱ መሳካት ቅድሚያ በመስጠት መስራት ይገባል ብለዋል።
ፕሮጀክቱን በተያዘለት መርሃ ግብር ለመተግበር እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ቅድሚያ ሰጥቶ ሥራውን በተነሳሽነትና በቁርጠኝነት እንዲሰራም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሳስበዋል፡፡