የሀገሪቱን የልማት ዕቅድ ለማሳካት የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል

የሀገሪቱን የልማት ዕቅድ ለማሳካት የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል

የኢትዮጵያን የ2018 በጀት ዓመት የልማት ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል  አስታወቀ፡፡

የተቋሙ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በሀገራዊ የ2018 በጀት ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።

የበጀት ዓመቱን ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ያቀረቡት በተቋሙ የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ እንደገለፁት ዕቅዱ ዓለም አቀፋዊ፣ አህገራዊና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ አዝማሚያዎችን እና የሀገሪቱን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው።

በውይይቱ ላይ በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በማህበራዊ ልማትና የህዝብ አገልግሎት፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በሠላም፣ በፍትህ፣ በውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ዘርፎች ላይ ለማከናወን የተያዙ ሀገራዊ ዕቅዶችን በዝርዝር አቅርበዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ እና ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ኢኮኖሚው ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ኢንጂነር ውድነህ እንደጠቀሱት በበጀት ዓመቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎችንና የቱሪዝም ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት፣ የወጭ ንግድን ለማሳደግ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ሥራ ስምሪትን በማስፋፋት ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን አስተዳደርና አፈፃፀም ለማሻሻል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት ቅነሳ እና የገቢ ግብር አሰባሰብ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡

በበጀት ዓመቱ በገበያ ላይ የተመሰረተ የወለድ ምጣኔ ሥርዓት በመተግበር፣ የግብርና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማሳደግ እንዲሁም የገበያ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡

የወጭ ንግድን ለማሳደግ የኢነርጂ ዘርፉ የራሱ አበርክቶት እንደሚኖረውና በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከኃይል ሽያጭ 426 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ እና ሉዓላዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እንደምትሰራ ገልፀው ከተለያዩ ሀገራት ጋር እያደረገች ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል  ትስስርም በዲፕሎማሲ ሥራዎች ላይ አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡

በዕለቱ ከዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት፣ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር፣ ከመሰረተ ልማት ግንባታ ፍትሃዊነት፣ ከግብርና ግብዓት አቅርቦት፣ ከሰላምና ፀጥታ፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ ከፕሮጀክት አፈፃፀም፣ ከመንግሥት ሠራተኛ የገቢ ግብር አተገባበር፣ ከፍትህ ሥርዓት እና ከመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጋር የተያያዙ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከተሳታፊዎቹ ቀርበዋል፡፡

ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደተናገሩት ውይይቱ ሠራተኛውን የዕቅዱ ባለቤት በማድረግ ወደ ውጤት ለመቀየር ያስችላል፡፡

የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሻሻል ውስጣዊ ችግሮችን በመፍታት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ያነሱት አቶ ሙላት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት የግል አልሚዎችን በማሳተፍ እየሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

በተቋሙ የኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ውድነህ የማነ በበኩላቸው በመንግሥት ለተያዙ ዕቅዶች የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል በአግባቡ ለማቅረብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የግል ባለሃብቱ በኃይል ልማት ዘርፉ ላይ እንዲሳተፍ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ለማሳደግ እንደሚረዳም ነው ኢንጂነር ውድነህ የተናገሩት፡፡

የኑሮ ውድነትን ለማቃለል መንግሥት ምርታማነትን ማሳደግ እና ዋጋ ማረጋጋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

በተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደጉማ ነዳ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ የሚከናወኑ ሥራዎችን በውስጥ የፋይናንስ አቅም ለመሸፈን የገቢ ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ ያስገድዳል፡፡

እንደ ሀገር የተያዘውን የልማት ዕቅድ ለማሳካት በፕሮጀክቶች አስተዳደርና አፈፃፀም ላይ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም የሥራ ኃላፊዎቹ አሳስበዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top