የራይቱ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ከደንበኞች የሚቀርቡ የኃይል ጥያቄዎችን የመመለስ አቅም እንዳለው የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው ሙሉጌታ አስታወቁ፡፡
የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ እንደገለፁት ጣቢያው 63 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር፣ ሦስት ሻንት ሪያክተር እንዲሁም አራት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አሉት፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው ከመልካ ዋከና ማመንጫ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ በባለ 230 ኪሎ ቮልት ለጎዴ ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም በባለ 33 ኪሎ ቮልት ለምስራቅ ባሌ ዞን እና ለሶማሌ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ኃይል እንደሚያቀርብ ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
በአካባቢው የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ማከፋፈያ ጣቢያው መጫን ከሚችለው 50 ሜጋ ዋት ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው 25 በመቶ እንደማይደርስ ነው አቶ ይድነቃቸው የተናገሩት።

የራይቱ ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ
ማከፋፈያ ጣቢያው ተጨማሪ የኃይል ፍላጎት የማስተናገድ አቅም እንዳለው የገለፁት ሥራ አስኪያጁ በአካባቢው ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በቂ እና ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ ጣቢያው ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
በጣቢያው ያሉት አራት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እስከ 25 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ቢኖራቸውም አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙት ሦስት ወጭ መስመሮች እየቀረበ ያለው ኃይል ግን 3 ነጥብ 34 ሜጋ ዋት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


በማከፋፈያ ጣቢያው የኦፕሬሽን ሠራተኛ የሆኑት አቶ ሽታው ኑርልኝ በበኩላቸው ጣቢያው በምስራቅ ባሌ ዞን ስር ለሚገኙት ለጊኒር ከተማና አካባቢው፣ ለራይቱና ዳዌ ሰረር ወረዳዎችና በስራቸው ለሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች እንዲሁም ለሶማሌ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች ኃይል እያቀረበ ይገኛል፡፡
ጣቢያው ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው በመረዳት የሚመለከተው አካል በአካባቢው ኢንቨስትመንትን በመሳብ የኃይል ተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የራይቱ የደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደበበ ዳዲ እንደገለፁት የራይቱ ማከፋፈያ ጣቢያ ያለውን አቅም ለመጠቀም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ በዚህም የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞችን ለመሳብ ከመስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑም አስታውቀዋል፡፡
የራይቱ ማከፋፈያ ጣቢያ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለከተሞች መስፋፋት፣ ለመሰረተ ልማቶች መስፋፋት እና ለማህበረሰቡ የአኗኗር ዘይቤ መሻሻል ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡ በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘው ይህ ማከፋፈያ ጣቢያ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

