ሪጅኑ በበጀት ዓመቱ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ስኬታማ ሥራዎችን አከናዉኗል

ሪጅኑ በበጀት ዓመቱ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ስኬታማ ሥራዎችን አከናዉኗል

በሪጂኑ ባሉ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮች የተቀናጀ እና የተናበበ ሥራ በመሰራቱ በበጀት ዓመቱ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ማስቻሉን የሰሜን ምስራቅ ሪጅን ሁለት አስታወቀ፡፡

የሪጂኑ ዳይሬክተር አቶ ሐሰን ሙሃመድ እንደተናገሩት ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩ መስመሮችን ወደ ጂ.አይ.ኤስ. ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ስርዓት መቀየር፣ የሲቪል እና የኤሌክትሮ መካኒካል፣ የፍተሻና ጥገና ስራዎች እንዲሁም የመስሪያ ቁሶችን የማሟላት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በተጨማሪም በመረጃ አያያዝና ኦፕሬሽን ዙሪያ ለሠራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዲሁም የመሠረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር የወይይት መድረኮችን ማካሄድ በበጀት ዓመቱ ታቅደው ሙሉ ለሙሉ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ናቸው፡፡

ይህም በሪጅኑ የተቀናጀና የተናበበ የአሰራር ስርዓት ከመፍጠሩም በተጨማሪ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቀርብ አስችሏል፡፡

በየጊዜው እያደገ የመጣው የኃይል ፍላጎት ለማሟላት በቀጣይ 2018 በጀት ዓመት የሰመራ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን አቅም የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወን የጠቆሙት አቶ ሐሰን ሪጅኑ እያንዳንዳቸው 230 ኪሎ ቮልት መጠን ያላቸውን  የሰመራ፣ ዲቼቶ እና አፍዴራ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና ከ436 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸውን የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እንዲሁም 988 የብረት ምሰሶዎችን ያስተዳድራል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top