በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መልካም አስተዳደርን በዘላቂነት ለማስፈን በኮርፖሬት ገቨርናንሰ እና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ ሥር የሚገኙ መምሪያዎች በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የዘርፉ ሥራ አስፈፃሚ አሳሰቡ፡፡
በዘርፉ ሥር የሚገኙት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን፤ የህግ አገልግሎት፤ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ እንዲሁም የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያዎች በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወኗቸውን ሥራዎች አቅርበው ተገምግሟል፡፡

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ በተቋሙ የሚገኙ ሴት ሠራተኞች መብትና ጥቅም ለማስከበር እና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት መንቀሳቀሱን ሲገልጽ የህግ አገልግሎት መምሪያ በበኩሉ የተቋሙን ጥቅም የሚያስጠብቁ የፍትሐብሔር፣ የሥራ ክርክር እና የካሳ ጉዳዮችን በመከታተል የመርታት አቅሙን ማሳደጉን ገልጿል፡፡

የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የተቋሙን ገጽታ ለመገንባት የሚያስችሉ መረጃዎችን በተለያዩ የግንኙት አግባቦች ተደራሽ እያደረገ ቢሆንም የግብአት አቅርቦት እንዲሟላለት ጠይቋል፡፡

የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ መምሪያ በበኩሉ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን ለመዋጋት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መስራቱን አስታውቋል፡፡

የመምሪያዎቹን ሪፖርት ተከትሎ በሠራተኞች ጥያቄና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን የግምገማውን ማጠቃለያ አቅጣጫ የሰጡት ሥራ አስፈፃሚው አቶ ዱጉማ ነዳ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ በማጎልበት፤ ያልተከናወኑ ተግባራትን በቀጣይ ስድስት ወራት በዕቅድ ውስጥ አካቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


በሁሉም መምሪያዎች ካለፈው ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ቢመዘገብም ተቋሙ ከሰነቀው ራዕይና ተልዕኮ አንፃር ሲታይ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ነው የገለፁት፡፡
በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ የስራ ዘርፎችን የአሰራር ሥርዓት ከመፈተሽ አንፃር ባለፉት ስድስት ወራት በዋና መስሪያ ቤት፣ በሪጅኖች እና በኃይል ማመንጫዎች ምልከታ ማድረግ መቻሉ ስኬታማ ጅማሮ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ድጉማ ገለፃ በፍትሐብሔር የክስ ጉዳዮች ላይ የመርታት አቅምን ለማሳደግ መረጃዎችን የማደራጀት እና የመያዝ አቅምን ማጎልበት ይገባል፡፡
ብልሹ አሰራር እና ሙስናን ለመከላከል የሥራ ዘርፎች እና በስራቸው የሚገኙ የስራ ክፍሎች ሥራዎችን በህግና በመመሪያ መሠረት እያከናወኑ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ከሁሉም የሥራ ዘርፎች ጋር በቅንጅት መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡
የተቋሙን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስከበር ዘመናዊ የዶክመንቴሽን ስራ ማከናወን እንደሚገባም ነው በአንክሮ የገለፁት፡፡
ፕሮጀክቶች ብዙ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስባቸው መሆኑን የገለፁት ስራ አስፈፃሚው እነዚህ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና በጀት ይጠናቀቁ ዘንድ በዘርፉ ስር የሚገኙ ሁሉም መምሪያዎች ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ዱጉማ ገለፃ መልካም አስተዳደር የሰፈነበት እና አገልጋይነትን ባህሉ ያደረገ ተቋም እውን ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እና ተናቦ መስራት ያስፈልጋል፡፡
በሁሉም መምሪያዎች የሚያስፈልጉ ግብአቶችን በመለየት በፍጥነት ማሟላት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



