በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል የተዘረጋው ስትራቴጂ ውጤት እያመጣ መሆኑን በተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት፣ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ ገለፀ፡፡
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ከሊል ሽፋ እንደገለፁት ባለፉት ስድስት ወራት በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ይፈፀም የነበረው ስርቆት ካለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የመቀነስ አዝማሚያ ታይቷል፡፡
በ12 ሪጅኖች የቀድሞ የመከላከያ መኮንኖችን በመመደብ የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በ5 ሪጅኖች የሚገኙ 12 የማስተላለፊያ መስመሮች ላይ 1 ሺህ 411 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን በአካባቢው ማህበረሰብ ለማስጠበቅ በዕቅድ ተይዞ 1 ሺህ 297 ምሰሶዎች ላይ ጥበቃ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ከሊል ገለፃ በአሁን ወቅት በሙከራ ደረጃ ጥበቃ እየተደረገላቸው ከሚገኙ 29 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች መካከል በ28ቱ ላይ ስርቆት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወንጀለኞች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በማዕከላዊ አንድ፣ ደቡብ አንድ እና ሁለት ሪጅኖች ተደጋጋሚ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆት ሲፈፀምባቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅ እና ምዕራብ ሪጅኖች ባለፉት ስድስት ወራት ከኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደነበሩ ገልፀው ሥራዎቹን ለማከናወንም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የኃይል መሰረተ ልማት ስርቆትን አስመልክቶ ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሰራቱንም አብራርተዋል፡፡
በመምሪያው የተቋማዊ መሰረተ ልማት ደህንነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍራፊስ በቀለ በበኩላቸው በተለያዩ አካባቢዎች ሲካሔዱ የቆዩት የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች ማህበረሰቡ መሰረተ ልማቶቹን በእኔነት ስሜት እንዲጠብቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡
በቀጣይም የታየውን መሻሻል አጠናክሮ ለማስቀጠል ከሚመለከታቸው የክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ እንዲሁም የየአካባቢው ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በትብብር እንደሚሰራም ነው የገለፁት፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

