በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ገቨርናንሰ እና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በስር የሚገኙ ሁሉም የሥራ ክፍሎች ሥራዎችን በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው የዘርፉ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዱጉማ ነዳ አሳስበዋል፡፡
በዘርፉ ሥር የሚገኙት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን፤ የህግ አገልግሎት፤ የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ እንዲሁም የሴቶች፣ ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ያከናወኗቸውን ሥራዎች ከሥራ ክፍሎቹ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በዛሬው ዕለት ገምግመዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት በየሥራ ክፍሎቹ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የነበሩ ጠንካራ ጎኖች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች በዝርዝር ቀርበዋል፡፡
በሥራ ክፍሎቹ የቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተዉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑት ተግባራት የተቋሙን ገጽታ በመገንባት፣ ተጠያቂነት፤ ግልጽነት እና ፍትሀዊነት በማስፈን ረገድ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡
ሥራ አስፈፃሚው በሰጡት የማጠቃለያ አቅጣጫ እንዳመለከቱት ተቋሙ የጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል፣ የተቋሙን ጥቅም ለማስጠበቅ እና ገጽታ ለመገንባት በሚያስችል መልኩ ለመቃኘት እንደዚህ ዓይነት የግምገማ መድረኮች ጥቅማቸው የጎላ ነው፡፡
ተቋሙ እያካሄደ ያለዉ ለውጥ ውጤታማ እንዲሆን ከዘርፉ ብዙ እንደሚጠበቅ በመገንዘብ በቀጣይም ለውጡን ውጤታማ ለማድረግ በተቀመጡ ደንቦችና አሰራሮች መሰረት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እንደ አቶ ዱጉማ ገለፃ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነበሩ መልካም ጎኖችን በማጠናከርና ደካማ ጎኖችን በማሻሻል መምሪያዎች በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል፡፡
ከአሰራር መመሪያዎች ጋር በተያያዘ በሥራ ክፍሎች የተነሱ ሃሳቦችን በግብዓትነት በመውሰድ መመሪያዎችን በማዘጋጀትና በማስፀደቅ ወደ ሥራ ለማስገባት የሥራ ክፍሎች ጋር በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘርፉ የጀመረውን የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው የሥራ ክፍሎች የሚበረታቱበት የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ጠቁመዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




