ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ የማከፋፈያ ጣቢያ መቆጣጠሪያዎች ወይም ስዊች ጊሮች በተቋሙ የውስጥ አቅም መቀየራቸው በጣቢያዎቹ የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን እንደሚያስችላቸው በቅየራ ሥራው ላይ የተሳተፉ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ፡፡
በደቡብ አንድ ሪጅን የማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና ጥገና የሥራ ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ያለው አማረ እንደተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያ መቆጣጠሪያዎችን የማዘመኑ ሥራ በቴክኖሎጂው ዙሪያ ስልጠና የወሰዱ የሪጅን ማስተባበሪያ እና የሪጅን የጥገና ባለሙያዎችን በማቀናጀት ሲከናወን ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት ከተከናወኑ የማዘመን ሥራዎች የተገኙ የእውቀትና የቴክኖሎጅ ሽግግሮችን በመጠቀም በአሁኑ ወቅት የመቆጣጠሪያ ቅየራ ሥራው በሪጅኑ የጥገና ባለሙያዎች እና በማከፋፈያ ጣቢያ ሠራተኞች እየተከናወነ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
የማዘመን ሥራው በተቋሙ የራስ አቅም መከናወኑ ሠራተኞቹ ቴክኖሎጂውን ተላምደው የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በቀላሉ እንዲያከናወኑ ለማድረግ እንደሚያግዝም አመልክተዋል፡፡
የሻሸመኔ ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምህረቱ ግዛው እና የይርጋለም ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈይሰል ዋቤ በበኩላቸው ከጣቢያዎቹ የብሬከር ቅየራ ሥራ ከኦፕሬሽን ሥራው ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ተግባራትን በአግባቡ ለመፈፀም የሚያስችል እውቀትና ክህሎት እየተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ ቁጥር አንድ ማከፋፈያ ጣቢያ የኦፕሬሽን ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ እቴነሽ አሎንጄ በበኩላቸው በብሬከር ቅየራ ሥራው መሳተፋቸው የኦፕሬሽን ሥራዎችን ለማቀላጠፍ እና ለሚያጋጥሙ ቴክኒካል ችግሮች በቀላሉ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ክህሎትና ግንዛቤ መቅሰማቸውን አስረድተዋል፡፡
በደቡብ አንድ እና ሁለት ሪጅኖች የጥገና ባለሙያ የሆኑት አቶ ዘውዴ ጥላሁን እና አቶ አስቻለው ጴጥሮስ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በሪጅኖች አቅም እየተከናወነ ላለው ሥራ ከዚህ በፊት ከዋና መስሪያ ቤት ሠራተኞች ጋር በመተባበር ከተከናወነው ሥራ የተገኘው የእርስ በእርስ መማማር እና ልምድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡
በራስ አቅም እየተከናወነ ያለው የመቆጣጠሪያዎች ቅየራ ሥራ በቀጣይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በራስ ባለሙያዎች መስራት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





