በሪጅኑ በኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀመው ስርቆት 90 በመቶ ቀንሷል

በሪጅኑ በኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀመው ስርቆት 90 በመቶ ቀንሷል

የምስራቅ ሁለት ሪጅን የኃይል ማስተላለፊያዎችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ በጅግጅጋ ከተማ ሲያካሂድ የቆየውን የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ አጠናቀቀ።

የሪጅኑን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ያቀረቡት በሪጅኑ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወርቁ ሙሉ እንደገለፁት ሪጅኑ አምስት የተለያየ የኪሎ ቮልት መጠን ያላቸውን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እያስተዳደረ ይገኛል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ1 ሺህ 643 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች እና 719  ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የቁጥጥር እና ጥገና ሥራዎች መከናወናቸውን እንዲሁም በጅግጅጋ ማከፋፈያ ጣቢያ የ33 እና 15 ኪሎ ቮልት የጂ.አይ.ኤስ ስዊችጊር ቅየራ ሥራ መከናወኑንም በሪፖርቱ አንስተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሪጅኑ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል ከሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና ሐረሪ ክልሎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን የገለፁት አቶ ወርቁ በዚህም ምክንያት አንድም የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ካለመውደቁም ባሻገር በሪጅኑ ያለው የስርቆት መጠን 90 በመቶ መቀነሱን ጨምረው ጠቅሰዋል።

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ አብዱላሂ አብሽር በግምገማው ማጠናቀቂያ ላይ እንደተናገሩት ለህብረተሰቡ ያልተቆራረጠና አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በአራተኛው ሩብ ዓመት የሪጅኑ ዕቅዶች ለማሳካት ሁሉም የሪጅኑ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top