
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን የሲቪል ጥገና ሱፐርቪዥን ቢሮ በራስ አቅም ባከናወነው የመንገድ ሥራ ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳኑን አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ደበላ እንደገለጹት በጊቤ አንድ እና በጊቤ ሁለት የሚገኙት የጠጠር መንገዶች በመጎዳታቸው የዕለት ከዕለት የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
በጊቤ አንድ የ11 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እና በጊቤ ሁለት የውሃ መቀበያ ወይም ኢን ቴክ መግቢያ 5 ኪሎ ሜትር የሚሆኑ የጠጠር መንገዶቹን ለመጠገን በ98 ሚሊዮን ብር ለኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ተሰጥቶ ነበር ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ኮርፖሬሽኑ ከስምምነቱ በኋላ የዋጋ ማሻሽያ ማድረግ በመፈለጉ የቀጥታ ግዢው እንዲሰረዝ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የቀጥታ ግዥው ከተሰረዘ በኋላ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስፈላጊ ማሽነሪዎችን በመከራየት ሥራው በሲቪል ጥገናና ሱፐርቪዥን ቢሮ ባለሙያዎች እንዲሰራ በመወሰን ወደ ሥራ መገባቱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በሲቪል ጥገና ሱፕርቪዥን ቢሮ እየተከናወነ ያለው የሁለቱ መንገዶች አፈጻጸም አሁን ላይ ከ98 በመቶ በላይ መድረሱን አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ የመንገድ ሥራው በክፍሉ ሠራተኞች መከናወኑ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን አቅርቦት ከነበረው ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ከማዳኑም በተጨማሪ ተቋሙ የባለሙያዎቹን አቅም እንዲጠቀም እና የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡
ቀሪ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ብርሃኑ የመንገዶቹ መጠናቀቅ የጣቢያዎችን የየዕለት ኦፕሬሽን ሥራዎች የተሳለጡ እንዲሆኑና ለሰራተኛው ምቹ የሥራ ከባቢን የሚፈጥር መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



