በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ ሲከናወን የቆየው የጥገና ሥራ ተጠናቀቀ

በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ ሲከናወን የቆየው የጥገና ሥራ ተጠናቀቀ

የአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የተንሸራታች መሬት መከላከያ ግንብና የመንገድ ጥገና ሥራዎች መጠናቀቃቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኮንስትራክሽን የራስ ኃይል ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ፡፡

በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ ውስጥ ሲከናወኑ የቆዩት የአፈር መናድ መከላከያና የመንገድ ጥገና ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አስመልክቶ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል።

በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ገለፃ ያደረጉት በመምሪያው የሲቪል ሥራዎች ጥገና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ግርማ መንገሻ እንደገለፁት በጣቢያው የተገነባው የተንሸታራች መሬት መከላከያ ግንብ ሥራ 110 ሜትር ርዝመትና 10 ሜትር ከፍታ አለው፡፡

በጣቢያዎች ውስጥ 125 ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ጥገና ሥራ መከናወኑንም ነው ሥራ አስኪያጁ በጉብኝቱ ወቅት የገለፁት።

የግንባታ ሥራውን በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ከኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ጽ/ቤት ጋር ኮንትራት ተፈርሞ ሥራው ቢጀመርም በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች በታሰበው ፍጥነት ግንባታውን ማከናወን እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ ዐለታማ መሆኑና የተለያዩ ከባድ ማሽነሪዎችን መጠቀም የግድ ሆኖ መገኘቱ ፕሮጀክቱን ፈታኝ አድርጎት እንደነበር ነው ኢንጅነር ግርማ የገለፁት።

የአዋሽ ወንዝ በፈጠረው የመሬት መንሸራተት ሳቢያ የጣቢያው ሠራተኞች ከመኖሪያ ቤት ወደ ኃይል ማመንጫ ቤት ተንቀሳቅሰው ለመስራት ተቸግረው እንደነበር ነው የጠቀሱት።

ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽ እና የኢንጅነሪንግ ዘርፎች ለነበራቸው ቀና ትብብርና ቅንጅት ምስጋና ያቀረቡት ኢንጂነር ግርማ ፕሮጀክቱ የራስ ኃይል ኮንስትራክሽን መምሪያ በኃይል ማመንጫዎች እያከናወናቸው ከሚገኙ የጥገና ሥራዎች ውስጥ ትልቁ መሆኑን ለጎብኚዎች አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውዱ ሸንቁጤ በበኩላቸው
በወቅቱ የነበረው የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናርና የግንባታ ማሽነሪዎች ተደጋጋሚ ብልሽት ሥራውን በተያዘው የጊዜ ገደብ አጠናቆ ለማስረከብ ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በኃይል ማመንጫ ጣቢያው የተንሸራታች መሬት መከላከያ ግንብና የመንገድ ጥገና ሥራዎችን ለማከናወን ከ4 ሺህ 500 በላይ ኩንታል ሲሚንቶ መጠቀማቸውንም ነው የገለፁት።

እንደ አቶ ዘውዱ ገለፃ ፕሮጀክቱን አጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከአዲስ አበባ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙት የአዋሽ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እያንዳንዳቸው 32 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አላቸው።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top