ከፕሮጀክቱ ልምድና ዕውቀት ለመቅሰም የሚያስችል አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው

ከፕሮጀክቱ ልምድና ዕውቀት ለመቅሰም የሚያስችል አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው

ከኮይሻ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ምርጥ ተሞክሮ ለመቅሰምና ዕውቀት ለመለዋወጥ የሚያስችል አውደ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዕውቀት አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ አለማየሁ እንደገለፁት አውደ ጥናቱ በፕሮጀክቱ እየተተገበሩ የሚገኙ አሰራሮችን በመመልከት ምርጥ ተሞክሮዎችንና ዕውቀቶችን ወደ ሌሎች ፕሮጀክቶች እና የሥራ ክፍሎች ለማካፈልና ለማስፋፋት ያለመ ነው።

አውደ ጥናቱ በፕሮጀክት አስተዳደር፣ በሠራተኞች የመኖሪያ ካምፕ አደረጃጀትና አስተዳደር፣ በአካባቢያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ ጥናት አፈፃፀም፣ በካሳ ክፍያና መልሶ ማቋቋም፣ በፕሮጀክት አፈፃፀም፣ ክትትልና ቁጥጥር፣ በቡድን ግንባታ፣ በሥራ ላይ ጤናና ደህንነት፣ እንዲሁም በማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር አስረድተዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ አውደ ጥናቱ  የዕውቀት ሽግግርን ለማጠናክር፣ የተሻሉ የሥራ አፈፃፀም ዘዴዎችን ለማስፋፋት፣ የሠራተኞችን ብቃት ለማሳደግ እና ተቋማዊ ዕውቀትን ለመጠበቅ የሚያግዙ ልምዶችን ለማግኘት ያስችላል።

በተጨማሪም ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለየትና ሰንዶ ለማስቀመጥ፣ የፕሮጀክት ጥራትንና ቁጥጥርን ለማሻሽል እንዲሁም የተቋሙን የዕውቀት አስተዳደር ሥርዓትን ለማጠናከር የሚያስችል ልምድና ዕውቀት ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት የተለያዩ ውይይቶች እና በፕሮጀክቱ የሥራ ቦታዎች የመስክ ምልከታ እንደሚካሄድ የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው በፕሮጀክቱ ላይ ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችናን ዕውቀቶችን ወደ ሥራ ቦታቸው በመውሰድ መተግበር እንዲችሉ በንቃት መሳተፍና መረጃዎችን በአግባቡ መያዝ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በልምድ እና የዕውቀት ልውውጥ መርሃ ግብሩ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮን ጨምሮ ከተቋሙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችና የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

Scroll to Top