የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሴት ሠራተኞች ቅድመ ምርመራ በማድረግ ከጡት ካንሰር ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ ቀረበ፡፡
የጡት ካንሰርን በቅድመ ምርመራ በጊዜ ማወቅ ሕይወትን ለማዳንና የስኬታማ ሕክምና ዕድልን ለማሳደግ ወሳኝነት አለው፡፡
የፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ማዕከል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመተባበር የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወርን ምክንያት በማድረግ በቅድመ ካንሰር ምርመራና መከላከል ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደ።
በፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ማዕከል የቅድመ መከላከል እና ክሊኒካዊ የአመጋገብ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ብርክቲ ማስረሻ በግንዛቤ ማስጨበጫው ላይ እንደተናገሩት የጡት ካንሰር መከላከል ለሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ባለመሆኑ የእያንዳንዱን ሰው የጤና ሁኔታ እና የስጋት ደረጃ በመለየት መከታተል ያስፈልጋል።

ሴቶች ለጡት ካንሰር ያላቸው የስጋት ደረጃ እንደሚለያይ ያመለከቱት ዶክተሯ በእናት ወይም በአባት በኩል ያለው የካንሰር የቤተሰብ ታሪክ፣ የዘረመል ሁኔታዎች እና ከዕድሜ መጨመር ጋር ተያይዘው የሚመጡ ለውጦች የስጋት ደረጃውን ለመገምገም ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሴቶች የአኗኗር ዘይቤያቸውን በማስተካከል ከጡት ካንሰር ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ ያመለከቱት ዶ/ር ብርክቲ አልኮል መጠጥን መቀነስ ወይም ማቆም፣ አዘውትሮ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ጤናማ የሰውነት ክብደትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የጡት ካንሰርን በጊዜ ለመለየትና ሕይወትን ለማዳን ከ40 ዓመት ዕድሜ በኋላ የጡት ራጅ(ማሞግራፊ) ምርመራ መጀመር፣ በየወሩ የጡት ራስን ምርመራ ማከናወን እና መደበኛ የሕክምና ክሊኒክ ምርመራዎችን ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጤና አገልግሎት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሠረት ሙሉጌታ በበኩላቸው የመድረኩ ዋና ዓላማ የተቋሙ ሴት ሠራተኞች ስለ በሽታው ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የቅድመ ምርመራ ባህልን ማስፋፋትና በሕመሙ ለተጎዱ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር በሴቶች ላይ ከሚሰነዘሩ የካንሰር ዓይነቶች መካከል ዋነኛው መሆኑን የጠቆሙት ወ/ሮ መሠረት አብዛኞቹ ታካሚዎች ወደ ሕክምና ማዕከላት የሚመጡት በሽታው ስር ከሰደደ በኋላ በመሆኑ ታክሞ የመዳን ዕድላቸውን አጥብቦታል ብለዋል።
በመሆኑም ሴት ሠራተኞች ተቋሙ የሚያመቻችላቸውን የቅድመ ምርመራ ዕድሎች በመጠቀም አስፈላጊውን ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባና ሕመሙን በጊዜ በመለየት መዳን እንደሚቻል አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።



የቢሮው ረዳት ሥራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ ተኽልቁ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የጡት ካንሰር ሥርጭት ለመግታት፣ የተቋሙ ሴት ሠራተኞች የቅድመ ምርመራና የሕክምና ክትትል እንዲያገኙ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተቋሙ ሴት ሠራተኞች በየጊዜው የጤና ሁኔታቸውን በመከታተል የጡት ራጅ ምርመራን ጨምሮ ሌሎች የጤና ክትትሎችን ማድረጋቸው በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
የዘንድሮው የዓለም የጤና ድርጅት የጡት ካንሰር መከላከል ንቅናቄ «እያንዳንዱ ታሪክ ልዩ ነው፤ እያንዳንዱ ሂደትም ዋጋ አለው!» በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።


