ተቋሙ የዲጂታል ሰነድ ማደራጃ ፖርታል ሥራ ሊያስጀምር ነው

ተቋሙ የዲጂታል ሰነድ ማደራጃ ፖርታል ሥራ ሊያስጀምር ነው


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተቋሙ የሚገኙ የአሠራር ሰነዶችን፣ መመሪያዎችን እና ፖሊሲዎችን በማዕከል ደረጃ ለማከማቸት፣ ለማደራጀት፣ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የሚያስችል «ኢ.ኢ.ፒ ሴንትራል ፖርታል» (EEP Central Portal) የተሰኘ ዘመናዊ የዲጂታል ሥርዓት በራስ አቅም አልምቶ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩን የተቋማዊ ለውጥ ቢሮ አስታወቀ።
 
ቢሮው የዲጂታል ሰነድ ማዕከሉን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ሥልጠና ከዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ለተውጣጡ ባለሙያዎች ሰጥቷል፡፡
 
ለባለሙያዎቹ ሥልጠናውን የሰጡት የኮር ፕሮሰስና ፖሊሲ ማኔጅመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ ለማ ከፍያለው እንደገለፁት የዲጂታል ሥርዓቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት በመሆኑ የሰነዶቹ ሚስጥራዊነትና ደህንነት ሙሉ በሙሉ ተጠብቆ ተጠቃሚዎች በሥራ ኃላፊነታቸውና በተፈቀደላቸው የሥልጣን ገደብ ብቻ ሰነዶችን እንዲያገኙ የሚያስችል ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት የተዘረጋበት ነው።
 
የዲጂታል ሰነድ ማዕከሉ ከኮር ፕሮሰስና ፖሊሲ ማኔጅመንት እና ከዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ በተውጣጡ ባለሙያዎች የተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ለማ የዲጂታል ሥርዓቱ ለተጠቃሚዎች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ ሆኖ መቅረቡንም አብራርተዋል።
 
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ሥርዓቱ ከቀላል የሰነድ ማከማቻነት ባለፈ ሠራተኞች በተለያዩ ቦታዎች ሆነው ሰነዶችን በጋራ እንዲያስተክሉ፣ እንዲወያዩ እና በትብብር ሥራዎችን እንዲያከናውኑ የሚያስችል አቅም አለው።
 

የዲጂታል ሥርዓቱ ወደ ሥራ መግባት የተቋሙን አጠቃላይ አፈፃፀምና የሀብት አጠቃቀም ውጤታማነት እንደሚያሻሽለው ገልፀው የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የዲጂታል አሠራር ሥርዓቱን በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተናግረዋል።
 
የዲጂታል ሰነድ ማዕከሉ በሚቀጥሉት ወራት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገባም አቶ ለማ ጠቁመዋል።
 
የተቋማዊ ለውጥ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ፍቅሬ እንደገለፁት የዲጂታል ሥርዓቱ ዋና ዓላማ በተቋም ደረጃ የሚዘጋጁ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ሰነዶች፣ የመንግሥት ፖሊሲዎችን እና የአሰራር ሂደቶች በአንድ ማዕከላዊ ቋት ውስጥ ለማስቀመጥ ነው፡፡
 
የዲጂታል ሥርዓቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የተለያዩ ሰነዶችን በሚፈልጉበት ጊዜ በቀላሉ እንዲያገኙና አገልግሎት ላይ እንዲያውሉ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

Scroll to Top