ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ከማሳደግ ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ታዳሽ ኃይል በማቅረብ የምሥራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ ትስስር እያጠናከረ መምጣቱ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ፖለቲካ ምሁሩና የሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ አባል የነበሩት ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) እንደገለጹት ሀገሪቱ እያደገ የመጣውን ታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅሟን በመጠቀም ለጎረቤቶቿ ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች።
ከኬንያ እስከ ታንዛኒያ በተዘረጋው የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለኬንያና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም ሀገሪቱ የምታመርተውን ንጹህ ኢነርጂ እስከ መካከለኛውና ደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ለማድረስ ትልቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅም ከፍተኛ መሆኑ የተጠቀሱት ምሁሩ ሀብቱን በሙሉ አቅም ለማልማት ግን ጊዜ የሚጠይቅና ደረጃ በደረጃ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።
ንጹህ ኢነርጂ በማመንጨት ትልቅ ድርሻ ያለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 14 ዓመታት መውሰዱን በማስታወስ ወደፊት የሚገነቡ ሌሎች ግድቦችም እንደ መጠናቸው አነስተኛ ወይም ረጅም ጊዜ ሊወስዱ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ታዳሽ የኃይል ሀብቷን ለቀጠናዊ ዕድገት ለማዋል ያላትን ዝግጁነት በተግባር ማሳየቷን የውሃ ፖለቲካ ምሁሩ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት የቀጣናውን የጋራ ተጠቃሚነት ከማሳደጉም በላይ በሀገራቱ መካከል ያለውን የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።